ማርም ሲበዛ ይመራል፤ የተጋነነ የራስ አረዳድ

በራስ መተማመን (self-confidence) ብዙዎቻችን እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የምንስማማበት እና ምናልባትም ስለሚያንሰን ብናሳድገዉ ብለን የምንመኘዉ እና የምንሰራበት ነገር ነው።  በዚህ ጽሁፍ ግን፣ የዚህን ተቃራኒ ስለሆነ እና ብዙዎቻችን ተጠቂ ስለሆንበት እና ምናልባትም ስለተጠቂነታችን እራሱ ግንዛቤው ስለሌለን፣ በእንግሊዘኛ “overconfidence bias”  (የተጋነነ የራስ አረዳድ ብየ ተርጉሜዋለሁ ነገር ግን የተሻለ የሚገልጸዉ ቃል ካለም በሃሳብ መስጫ ሳጥን ዉስጥ ብትነግሩኝ ደስ ዪለኛል) ስለሚባለው እጅግ አደገኛ እና በሰፊዉ በግለሰቦች ላይ እንደሚንጸባረቅ የስነ ልቦና ምርምር ዘርፍ ስለሚያሳየን የራስ አረዳድ ግድፈት ምንነት እና በዉሳኔዎቻችን ላይ ስለሚኖረው ሚና አነሳለሁ። 

ለምሳሌ፡- እራሳችንን የሚከተሉትን ነገሮች በሚመስል አስተሳሰብ ዉስጥ ምን ያክሉን ጊዜ እንደምናገኘው እናስብ፤ 

እኔ በ ኮሮና የመያዝ እድሌ በጣም አነስተኛ ነው። የማስታወስ ችሎታየ ከአብዛኛው ሰው ይሻላል። ከአብዛኛዉ የተሻልኩ ታታሪ ሰራተኛ ነኝ። ካብዛኛው የተሻለ ፈጣን አእምሮ አለኝ። ንግድ ብጀምር ባጭር ግዜ ስኬታማ እሆናለሁ። ከብዙዎች አንጻር ማህበራዊ ሚድያ ላይ የማገኛቸዉን መረጃዎቸ እዉነተኛነት በቀላሉ መለየት የምችል ሰው ነኝ። መኪና የመንዳት ችሎታየ ከብዙዎች የተሻለ ነው። የመረዳት ችሎታየ ከብዙዎች የተሻለ ነው። ስለሃገራችን ሁኔታ ካብዛኛው የተሻለ መረዳት አለኝ። ወዘተ። 

መልስዎ አብዛኛዉን ግዜ ከሆነ፣ የራስ አረዳዶዎን በጥርጣሬ ማየት ሊኖርቦት ይገባል። 

“Overconfidence bias” ማለት ስለ የራሳችን አቅም፤ ተሰጥኦ፤ እና ብቃት የተጋነነ አረዳድ  ሲኖረን ማለት ነው።በርግጥ፣ ስለ የራሳችን አቅም፤ ተሰጣኦ፤ እና ብቃት በትክክል ከሆነው እጅግ  ያነሰ አመለካከትም ሊኖረን ይችላል። ይህም “underconfidence” ወይም “ያነሰ የራስ አረዳድ” የሚባለው ነው። ምንም እንኳን ሁለቱም የየራሳቸው ጥቅም እና ጉዳት ቢኖራቸዉም  ጥናቶች የሚያሳዩት፣ የብዙዎቻችን ችግር የተጋነነ የራስ አረዳድ መኖር ስለሆነ እና ይህ አመለካከት በህይወታችን ዉስጥ በምንወስናቸዉ ዉሳኔዎች ላይ እጂግ ብዙ ምልከታዎች ስለሚኖሩት፣ ጽሁፌን በሱ ላይ እንዲያተኩር ላድርገዉ ፈለኩ። 

በመቀጠል፣ የተለያዩ የተጋነነ የራስ አረዳድ አይነቶችን ከተለያዩ በምርምር ከተገኙ ምሳሌዎች ጋር ላቅርብላችሁ፤

1.  “Over ranking” (በአማርኛ፣ ራስን ከፍ አድርጎ ማስቀመጥ) ይህ አይነት የተጋነነ የራስ አረዳድ ችግር እራስን ከሌሎች ጋር በማወዳደር የተሻለ ደረጃ ላይ እንደምንገኝ ማመን ማለት ነው። ለምሳሌ፡- በመግቢያው ላይ ከተዘረዘሩት መሃል፣ የማስታወስ ችሎታየ ከአብዛኛው ሰው ይሻላል። ከአብዛኛዉ የተሻልኩ ታታሪ ሰራተኛ ነኝ። ካብዛኛው የተሻለ ፈጣን አእምሮ አለኝ ወዘተ ብለን የምናስብ ከሆነ፣ ለራሳችን የተጋነነ ደረጃ እየሰጠን የመሆን እድላችን ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል ። ለምሳሌ፡- አንድ ቆየት ያለ ጥናት ግለሰቦችን የማሽከርከር ብቃታቸዉን ደረጃ እንዲሰጡት ይጠይቃቸዋል። የጥናቱ ዉጤት ሲያዩት ከ 77 እስከ 88 በመቶ በላይ መላሾች የማሽከርከር ብቃታቸዉ ከመካከለኛዉ  በላይ እንደሆነ የሚያምኑ እና አደጋ የማድረስ እድላቸዉም ከአብዛኛዉ ያነሰ ነው ብለው የሚያምኑ ሁነው ተገኙ። እነዚህ አሽከርካሪዎች ትክክለኛ የራስ አረዳድ ቢኖራቸው ኑሮ 50 በመቶ አካባቢ ብቻ መላሾች ነበር ከመካከለኛ በላይ ነን ባይ መሆን የነበረባቸው (በስታቲስቲክስ ጽንሰሃሳብ መሰረት የአነዳድ ብቃት መደበኛ ስርጭት (normal distribution) ይከተላል ተብሎ ይታመናል ስለዚህ ከመካከለኛዉ  በላይ ብቃት ያላቸዉ ግለሰቦች 50 በመቶ ያክሉ ብቻ ነው የሚሆኑት)። ይህ የሚያሳየን እንግዲህ ከ27 እስከ 38 በመቶዎቹ አሽከርካሪዎች ከሆኑት በላይ እንደሆኑ የሚያምኑ መሆናችሀዉን ነው። 

2. “Optimism bias” (በአማርኛ የተጋነነ ተስፈኛነት ልንለው እንችላለን) ይህ አይነት የተጋነነ የራስ አረዳድ ችግር ደግሞ ያለ በቂ ምክኒያት የተጋነነ ተስፈኛነት ሲኖረን እና በኛ ህይወት ላይ መልካም ነገሮች የመከሰት እድላቸው ከፍተኛ፣ መጥፎ ነገሮች የመከሰት እድላቸው ደግሞ አነስተኛ እንደሆኑ አድርጎ ማመን ማለት ነው። እንደዚህ አይነት ችግር ካለብን፣ ለምሳሌ፡- ነጋችን እጅግ በጣም ብሩህ እና አልጋ ባልጋ እንደሆነ ይሰማናል፤ ስለዚህ ዛሬ ላይ ለነገ የሚያስፈልጉንን ነገሮች አስበን የመስራት ሁኔታችን ዝቅ ያለ ይሆናል፤ ነገሮችን በፍጥነት እና በጥራት የመስራት ብቃት እንዳለን እናምናለን ለዚህም ስናቅድ ብዙ ስራ በ አጭር ጊዜ እናቅዳለን፤ መጥፎ (እንደ በሽታ፣ አደጋ፣ ፍቺ) ያሉ ነገሮች እኛ ላይ የመከሰት እድላቸዉ እጅግ ያነሰ እንደሆነ ይሰማናል ስለዚህም በቂ ጥንቃቄ የማድረግ እድላችን ዝቅ ያለ ይሆናል ወዘተ። ለምሳሌ፡- ሌላ ቆየት ያለ ጥናት የኮሌጅ ተማሪዎችን ተስፈኝነት ለመረዳት 42 የተለያዩ፣ መልካም (እንደ ጥሩ ስራ ማግኘት፣ ቤት መግዛት፣ ረጅም እድሜ መኖር ወዘተ)  እና መጥፎ (እንደ ፍቺ፣ ከስራ መባረር፣ በሽታ ወዘተ) የህይወት ሁነቶችን ከጓደኞቻቸዉ አንጻር በእነሱ ላይ የመድረስ እድላቸዉን እንዲገምቱ ያደርጋቸዋል። የጥናቱ ዉጤት ያሳየው፣ አብዛኞቹ ተማሪዎች መልካም ነገሮች በነሱ ህይወት ላይ የመከሰት እድላቸው ከጓደኞቻቸዉ አንጻር ከፍ ያለ እንደሆነ ሲያምኑ፣ መጥፎ ነገሮች በነሱ ህይወት ላይ የመከሰት እድላቸው ደግሞ ከጓደኞቻቸዉ አንጻር ያነሰ እንደሆነ የሚያምኑ እንደሆኑ ያሳያል። 

3. “Desirability effect” (በአማርኛ የምንፈልገዉ ዉጤት/ነገር የመሆን እድሉን አጋኖ የመመልከት ልንለው እንችላለን) ይህ የአረዳድ ግድፈት ደግሞ የሚኖረን የምንፈልጋቸዉ ነገሮች/ሁኔታዎችን የመሆን እድላቸዉን ከሆነው በላይ ከፍ ያለ እንደሆነ አርጎ የመረዳት/የማሰብ ሁኔታ ሲኖርብን ነው (ይህን ጥናት ይመልከቱ)። ለምሳሌ፡- የሆነን ጦርነት ማሸነፍ ስለምንፈልግ ብቻ የማሸነፍ እድላችን ላቅ ያለ እንደሆነ አርገን እናስባለን፤ የሆነን ስራ/የትምህርት እድል ማግኘት በጣም ስለምንፈልግ የማግኘት እድላችን እጅግ ከፍ ያለ ሆኖ ሊሰማን ይችላል፤ ፈተናን መድፈን/ጥሩ ዉጤት ማምጣት ስለምንፈልግ ብቻ ከፈተና ስንወጣ ጥሩ እንደሰራን ሲሰማን ማለት ነው።  ለምሳሌ፡- እኔ እራሴ የሰራሁትን አንድ ጥናት ላጋራ። አርሶ አደሮችን ሁለት አይነት ፈተና ሰጠኋቸዉ። አንደኛው ግብርና ነክ የሆኑ ጥያቄዎችን የያዘ ሲሆን ሌላኛዉ ደሞ አይተዉት የማያቁት ርእስ ላይ ያተኮረ (የስእሎችን አደራደር አይቶ የጎደለዉን መምረጥ የሚፈልግ፤ በኢንግሊዘኛ Raven’s matrices test የሚባለዉ ፈተና)። ፈተናዉን ከመጀመራቸዉ በፊት ምሳሌ እንዲሆናቸዉ ሁለት ጥያቄ አሳያቸዉ እና ተመሳሳይ 10 ጥያቄ ልሰጣቸዉ እንደሆነ እና ከአስሩ ምን ያክሉን በትክክል እመልሳለሁ ብለዉ እንደሚያስቡ ጠየኳቸዉ። ከዛ ትክክል የመለሱትን ከጠበቁት አንጻር ሳየዉ፣ የግብርናው ላይ 83 በመቶ መላሾች እመልሳለሁ ካሉት በታች ሲመልሱ፣ አይተዉት በማያቁት ርእስ ላይ ደግሞ 76 በመቶ መላሾች እመልሳለሁ ካሉት በታች ነው መመለስ የቻሉት። ይህም ማለት፣ ምሳሌዎቹን ካዩ በዉሃላ፣ ብዙዎቹ ጥያቄዋቹን የመመለስ አቅማቸዉን አጋነውት ነበር ማለት ነው። 

4. “Illusion of Control” (በአማርኛ  የራስ የቁጥጥር አቅም ብዥታ ልንለው እንችላለን) ይህ የአረዳድ ግድፈት ደግሞ አለብን የሚባለው በህይወታችን ዉስጥ የሚከናወኑ ነገሮችን የመቆጣተር አቅማችንን አግዝፈን ስንመለከት እና ስናምን ነው (ይህን የራስ የቁጥጥር አቅም ብዥታ ችግር ለመጀመሪያ ግዜ ያገኘውን ጥናት ይመልከቱ)። ይህም ማለት፣ ይሄን ይሄን ካደረኩ፣ እነዚህን እነዚህን ዉጤቶች አገኛለው፤ እነዚህን ነገሮች እስካደረኩ ድረስ፣ ዉጤቱን ከማግኘት የሚያግደኝ ነገር አይኖርም ብለን ጠንካራ አቋም ሲኖረን ማለት ነው። እንደዚህ አይነት አቋም ሲኖረን የምንዘነጋው ነገር አለም ላይ የተለያዩ (እኛ እንዳሉ የምናቃቸዉም የማናቃቸዉም) ሃይሎች በተለያየ ጥምረት እየሰሩ የኛ ህይወት ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳርፉ ነው። ሌላ ምሳሌ፡- ስራ ቦታ ላይ ጠንክሬ ከሰራሁ እና የሚጠበቅብኝን ሃላፊነት ከተወጣሁ፣ አለቃየ ጋር ጥሩ ግንኙነት ይኖረኛል፣ ከዛም የሚገባኝን እድገት አገኛለሁ ብለን ልናስብ እና ልንከዉን እንችላለን። ነገር ግን አለቃችን የኛን ጥረት የመረዳት ፍላጎት ላይኖረው፣ ቢኖረዉ እንኳ እዉቅና የመስጠት ፍላጎት ላይኖረው ይችላል። በዚህ ሁኔታ የአለቃችን ስሜት እና ፍላጎት ላይ ያለን ቁጥጥር እምብዛም ነው ማለት ነው። እንደዚህ አይነት የቁጥጥር አቅም ብዥታ፣ ለአላስፈላጊ እራስ ወቀሳ እና ለከባድ ብስጭት ሊዳርገን ይችላል።  ተመሳሳይ ችግሮች በተለያዩ የህይወታችን ክፍሎች ላይ ይከሰታሉ። 

ከላይ እንደተመለከትነው የተጋነነ የራስ አረዳድ ለተለያዩ ጎጂ ዉሳኔዋች እና ለብስጭት የሚዳርገን ከሆነ፣ ለምን በሰዎች ዘንድ በብዛት ሊኖር ቻለ? ምን ጥቅም ቢኖረው ነው? እስካሁን በዚህ ዙርያ ያለን እዉቀት እንደሚያሳየው ከሆነ፣ ለራሳችን የተጋነነ አረዳድ ሲኖረን (ያው የተጋነነ ነው ብለን ስለማናስብ፣ በትክክል አሉን የምንላቸዉ ነገሮች እንዳሉን ስለሆነ የምናምነው) የሚከተሉት ጥቅሞችን ስለሚሰጠን ነው ተብሎ ይታመናል። አንደኛ፡- ብቃት እና እውቀት አለን ብለን በማመን እና ያንን በማንጸባረቅ በዙርያችን ባሉ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነታችን ይጨምራል። ይህ ደግሞ በማህበራዊ ህይወታችን ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታል (ይህን ጥናት ይመልከቱ)። ሁለተኛ፡- ስለራሳችን ከትክክለኛው አመለካከት ይልቅ የተጋነነ አመለካከት በመያዝ የተሻለ እርካታን እናገኛለን ለዚህም አእምሮአችን እራሳችንን በበጎ እንድንመለከተዉ በሚያስችል መልኩ ነው ‘ፕሮግራም’ የተደረገው ማለት እንችላለን። ሶስተኛ፡-ስለራሳችን አቅም እና ብቃት ጠንካራ አመለካከት በመያዝ (ማድረግ እችላለው፣ ጥሩ አቅም አለኝ) ብለን በማሰብ ነው ስራዎችን የመከወን ፍላጎት (ሞቲቬሽን) የምናገኘዉ/የሚኖረን።  ካለዛ ብዙ ስራዎችን የመከወን ሞራል/ተነሳሽነት ላይኖረን ይችል ነበር ማለት ነው (ለነዚህ ነጥቦች ደግሞ፣ ይህን ጥናት ይመልከቱ)። አራተኛ፡- የተጋነነ የራስ አረዳድ እና የቁጥጥር ብዥታ ከእዉነታው የተሻለ ደስታ ይሰጠናል (ቢያንስ ለአጭር ግዜ)። ለምስሌ፡-በበሽታ የመያዝ እድላችን ትንሽ ነው ብለን ማሰብ የተሻለ እረፍት እና ደስታ ሲሰጠን፣ የመያዝ እድሌ ከፍ ያለ ነው ብሎ ከሚያስበው ይልቅ ለጊዘው የተሻለ እፎይታ እና እርካታን ይሰጠናል። 

ይህ  የሚያሳየን የተጋነነ የራስ አረዳድ እንደማንኛዉም ነገር ጠቃሚም ጎጂም ዉጤቶች አሉት ማለት ነው። ስለዚህ፣ ጠቃሚነቱን እያጣጣምን ጎጂነቱን እየቀነስን ለመጓዝ እና በእንደዚ አይነት እራስን በትክክል ካለመረዳት የሚመነጪ አሳሳች ዉሳኔዎችን ከማሳለፍ መከልከል እንችል ዘንድ፣ ሁሌም እራሳችንን እና ዉሳኔዎቻችንን በጤናማ ጥርጣሬ ማየት ሊጠቅመን ይችላል። እራሳችንን በሁኔታዎች ላይ በጣም እርግጠኛ፣ ተስፈኛ፣ አዋቂ ሁነን ስናገኘው፣ እንጠራጠረው። 

Please share this to:
Social media & sharing icons powered by UltimatelySocial