የተሻለ የታሪክ አረዳድ ለተሻለ አገር
የኢትዮጵያን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሂደት ለሚከታተል አንድ ነገር ግልጽ ይሆንለታል፡፡ ይኸውም የታሪክ አረዳዳችንን አንድ እርምጃ ካልወሰድን ኢትዮጵያን አንድ እርምጃ መውሰድ አንችልም። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ አንዱ ማቀጣጠያ ሆኖ የሚያገለግል ነገር ቢኖር የአገሪቷ ታሪክ ነው፡፡ የታሪክን ሚና ከአሉታዊ ወደ አዎንታዊነት የምንቀይርበት መንገድ ካልተፈጠረ የአገራችንን ችግር እና ቀውስ እልባት መስጠት አይቻልም። እንዲሁም ታሪክን አስተካክሎ መረዳት ወይም መተርጎም ማንነታችንን፣መንገዳችንና መዳረሻችንን እንደ ሀገር ለማጥራት ይረዳናል።
አንዳንዶቻችን ታሪክ ምን ይሰራል ለምን ዝም ብለን ወደ ልማት አንሄድም ልንል እንችላለን፡፡ ይህ ታሪክ በሰው ሕይወት ውስጥ ያለውን ጉልህ ሚና ካለመገንዘብ የመጣ ይመስለኛል፡፡ እስቲ እራሳችን በግል ሕይወታችን ውስጥ ያለንን ታሪክ ሁሉ እንርሳና ወደ ፊት ብቻ ለማሰብ እንሞክር፤ የሚቻል አይደለም፡፡ እኔ እከሌ ነኝ ብዬ እንኳን ስናገር የኔ ማንነት የሚገነባው ትላንት ላይ ባለፍኩበት ህይወት፥ የተማርኩት ትምህርት፥ ያፈራኋቸው ጓደኞች ወዘተ ነው፡፡ ትላንትን የምረሳ ከሆነ ቃልኪዳኔንም ፣ያበደርኩትንም፣የተበደርኩትንም እየረሳሁ ልቀጥል ማለት ነው፡፡ ትላንት የጀመርኩትን ካወቅሁ ዛሬ ላይ የምቀጥለውንም ለማወቅ ይረዳኛል፡፡ ስለዚህ ታሪክ እንደ አገር እኛ እንዲህ ነን ብሎ ለመናገር፥ እንደ አገር የጀመርነውን ለማስቀጠል አስፈላጊ ነው፡፡ ከዜሮ መጀመር አይቻልም ቢቻልም እንኳን ተመራጭ አይደለም። ምክንያቱም ከትላንት መማር ስላለብን፤ከትላንት ላይ መገንባት ስላለብን።
ሆኖም ታሪክን መረዳት ቀላል አይደለም፡፡ ታሪክ በጥንቃቄ ሊመረመር የሚገባው የእውቀት ዘርፍ ነው፡፡ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ግን የታሪክ ዕውቀት እንደ ተራ ወሬ ተቆጥሮ የማህበራዊ ሚዲያ ማድመቂያ እና የፖለቲካ የፕሮፓጋንዳ ተራ መሳሪያ ከሆነ ቆይቷል፡፡ እንዲህ ሲሆን ሚዛናዊ የሆነ የታሪክ አረዳድ ላይ ተደግፈን የተሻለ ነገን ከመገንባት ይልቅ የታሪክ እስረኛ እንሆናለን፡፡
በዚህ ጽሁፍ ታሪክን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ቁልፍ ያልኳቸውን ሶስት ሃሳቦች ወይም እይታዎች ለይቼ ለማውጣት እሞክራለው። እነኝህ ሃሳቦች የታሪክ አረዳዳችንን አንድ እርምጃ ለመውሰድ እንደ ግብአት ያገለግላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለው።
ሀ/ ታሪክና ትርክት
ታሪክን ከተራኪው ለይቶ ማየት ይከብዳል ምክንያቱም ታሪክ በተራኪው አተረጓጎም ላይ በእጅጉ ስለሚመሰረት፡፡ ታሪክን ሳስብ ብዙ ጊዜ የሚመጣብኝ የሕፃናት መጫወቻው ሌጎ (lego) ነው፡፡ ሕፃናት የሚሰካኩትን የሌጎ ጡቦች እየገጣጠሙ ሲፈልጉ ቤት ወይም ሰው ወይንም መኪና እየሠሩ ይጫወታሉ፡፡ አንድ ህፃን ተመሳሳይ ጡቦችን በመጠቀም የተለያየ ቅርጽ እንደ ፍላጎቱ ሊሰራ ይችላል። ልክ ግንበኛም የሚጠቀማቸው ጡቦች ቢመሳሰሉም የተለያየ ዓይነት ቤት ሊሰራ እንደሚችለው። የታሪክ አተራረክም ከዚህ ሁኔታ ጋር በጣም ይመሳሰላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ተራኪ አደን የወጣን ሰው ተመልክቶ ሚስትና ልጆቹን ለማስተዳደር ደፋ ቀና የሚል ባተሌ አድርጎ ሲያቀርበው ሌላ ተራኪ ደግሞ ሞፈር ለመጨበጥ የማይፈልግ ሰነፍ አድርጎ ሊስለው ይችላል፡፡ በተለይ ተራኪው የሰውዬውን ጎሳ እና ብሔር ወይም ሀይማኖት ካወቀ ትርክቱ ሌላ ጡዘት ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ በጠቅላላው ግን ሰዎች አንድን ትርክት ከፈጠሩ በኋላ ያለ በቂ ማስረጃ እውነተኛ አድርጎ የመቀጠል በዛ አስተሳሰብም የመወሰድ ዝንባሌ እንዳላቸው የተረጋገጠ ሀቅ ነው፤ ይህም የትርክት መዛባት (narrative fallacy) ይባላል፡፡ ለምሳሌ አደን የወጣውን ሰው ሰነፍ አድርጎ ያቀረበው ተራኪ የሰውየውን ቀዬ ለምነትና ምርታማነት እንዲሁም አንድ አዝማሪ እንዴት ቀዬውን በእርሻ እንዳወደሰው እየጠቀሰ ሲተርክና አደን የወጣውን ሰው ሲኮንን ስናነብ ከዛ ሌላ እውነት ወይም እይታ አለ ብሎ ለማሰብ ሊከብደን ይችላል። ታሪክ አንዴ በአንድ መልኩ ከተተረክ እንደአንዳች ድግምት የሚያፈዝ ፀባይ ይኖረዋል፤ ይህ ነው የትርክት መዛባት የሚሆነው።
ሆኖም ይህን ስል ተጨባጭ ታሪክ የለም ታሪክ ሁሌም እንደተመልካቹ ነው ለማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም አጽንዖት ለመስጠት የፈለኩት ታሪክ በባለሞያ ወይም በታሪክ ተመራማሪ በጥንቃቄ ሊመረመር የሚገባው እንጂ በግዴለሽነት ልንተርከው የማይገባ መሆኑን ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኩት አደን የወጣን ሰው በጥንቃቄ ሁኔታውን ስንመረምር አደን ለምን እንደወጣ ልንደርስበት እንደምንችል ሁሉ ታሪክም ጊዜን ሰጥቶ በጥልቀት ላጠናው በማስረጃ ሊተነተን የሚችል ተጨባጭ እውነታን ይዟል፡፡ ምንም እንኳን ለባለሞያም እንኳን የታሪክን ሰበብና ውጤት (cause and effect) ማወቅ እጅጉን ፈታኝ ቢሆንም።
ባለሙያ ያልያዘው ታሪክ ከታሪክ ቀመስ ልብ-ወለድ አይሻልም። ደፋር በተነሳ ቁጥር ልክ እንደ ሕፃናት መጫወቻው ሌጎ የወደድውን የታሪክ ቅርጽ የታሪክ ሁነቶችን እየገጣጠመ መሥራት ይችላል፡፡ በዚህ የአስተሳሰብ መነጽር ካየነው በየፖለቲካ መድረኩ እና በየማህበራዊ ሚዲያ የምናነባቸውን አብዛኞቹን ‹‹ ትርክቶች ›› ታሪክ ማለት አይቻልም ታሪክ ቀመስ ልብ-ወለድ እንጂ። በሌላ ጽንፍ ደግሞ የታሪክ ባለሙያዎች በፍፁም ሚዛናዊነት ታሪክን ይተርካሉ ማለት አይደለም። ማንነታቸውና የተለያዩ ሁኔታዎች አረዳዳቸውን ሊያዛቡ ይችላሉ፡፡ ቢያንስ ግን ሞያዊ አቀራረብን እስከተከተሉ ድረስ ይህንን መስመር ተከትሎ ለማረም የተሻለ ይቀላል፡፡ ልክ ፍሬን ያልበጠሰ መኪና መሰመር ቢስት እንኳን እንደምንም ብሎ የማቆም እድል እንደሚኖረው ሁሉ። መኪናው ፍሬን ከበጠሰ ግን ከባድ ነው!
ታሪክ በባለሙያ ተስተካክሎ ቢተረክም እንኳን ቢያንስ በሁለት እይታዎች ሊቀመም ይገባዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ በጊዜ አረዳድ እና በግለሰብ ማንነት።
ለ/ ታሪክና ጊዜ
ታሪክን ስናነሳ የጊዜ ጉዳይ ሁሌም አብሮ የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ታሪክ ስንል የነገንና የዛሬን ሳይሆን የትላንትን ወይም የድሮውን ጊዜ ብቻ ያመለክታል፡፡ ነገር ግን ትላንት የምንለው ጊዜ ከዚህ በፊት ዛሬ እና ነገ የተባለውን ነው፡፡ ስለዚህ ታሪክን ስናነሳ ትላንት ላይ ብናተኩርም ዛሬ እና ነገ ግን በታሪክነት ከትላንት አያንሱም ጊዜያቸውን የሚጠብቁ ታሪኮች ናቸውና።
ስለዚህ ታሪክን በመረዳት ውስጥ ቁልፍ ሃሳብ ሊሆን የሚገባው ታሪክ ዛሬንም ነገንም እንደሚያጠቃልል መረዳት ነው ቢዬ አምናለው።። ለምሳሌ እኛ ኢትዮጵያውያን ስለታሪካችን ስናነሳ ዛሬ እና ወደፊት የምንሰራውም የእኛው ታሪክ መሆኑን ማስተዋል ይኖርብናል። በ10ኛው ክ/ዘመን የነበሩ ኢትዮጵያውያን የላሊበላ ውቅር ቤተ ክርስትያናት ተሰርተው ባያዩአቸውም (ከ10ኛው ክ/ዘ በኋላ ስለተሰሩ) በኋላ ላይ ሲስሩ የኢትዮጵያዊ ታሪካቸው አካል ሆኗል። እኛም ዛሬ ላይ ያለን ኢትዮጵያዊያን ዛሬ እና ወደፊት የምንሰራው ታሪክ ካለፈው እኩል ታሪካችን ነው። ስለዚህ ታሪክ ያለፈና የተፈጸመ ብቻ ሳይሆን በእጃችን ያለ እንዲሁም እየተፈጸመ ያለና ልንቆጣጠረው የምንችል ነው ማለት ነው።
ይህ አይነቱ አስተሳሰብ በአሁኑ ሰዓት በአገራችንን የሚስተዋለውን አሉታዊ የሆነ የታሪክ አረዳድ አባዜ ለመግራት በጣም ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለው። ለምሳሌ በታሪክ ስለተጋጨን ግፋ ሲልም ደም ስለተፋሰስን አሁን አንድ ላይ አንኖርም ለሚሉ ፖለቲከኞች ታሪክ የትናንት ብቻ አይደሉም የነገም ነው ትናንት ብንጋጭም ዛሬ እና ነገ ወንድማማች ለመሆን ከመረጥን ምርጫችን ታሪካችን ይሆናል ብሎ መከራከር ይቻላል። የነገ ተስፋችን ወይም የነገ ታሪካችን ከትላንቱ እኩል ታሪካችን ስለሆነ። በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ አካባቢ የነበር ስልጣኔን በመጥቀስ የበላይነትን ለሚሰብኩ ፖለቲከኞች ደግሞ ትላንት የነበረውን ያህል መጨረሻው የማይታየው ረጅሙ መጪ ጊዜ ስልጣኔ ለመገንባት ከበቂ በላይ ነውና አትሳሳቱ ልንላቸው እንችላለን። የታሪክ መዝገብ አልተዘጋም ገና ክፍት ነው እና አስተውሉ ብለን ከትላንት የበለጠ ነገን በወንድማማችነት ልንገነባ እንደምንችል ማስረዳት ይቀላል።
በጥቅሉ ታሪክ የትናንት ብች አይደለም የዛሬም የነገም ነው ከጃችን የወጣውን ትላንት መማሪያ አድርገን ነገን የፍቅርና የልማት ታሪክ የማድረግ ምርጫ በእጃችን ነው።
ሐ/ ታሪክና ግለሰብ
ታሪክ ስንል ሁሌም የሚያመለክተው አንድን አገር ወይንም ማህበረሰብ ነወ። በመሆኑም ታሪክ ከቡድን ማንነት ጋር የተቆራኘ ነው። በአገራችን ያለውም የታሪክ አተራረክ ይህንን የቡድን ታሪከ የሰዎች የታሪክ ዕጣ ፈንታ አድርጎ ያቀርባል። ይህ አቀራረብ አንድ ትልቅ መዛነፍን ያመጣል። ይኸውም የግለሰብን ማንነት ማሳነስ ወይም መደፍጠጥ ነው። የምንመጣበት ማህበረሰብ ታሪክ ምንም ይሁን ምን መረሳት የሌለበት የግለሰብ ታሪካችንን ያክል እያንዳንዳችንን የሚወክል ታሪክ የለም። የመጣሁበት ማህበረሰብ ታሪክ በመሀንዲሶች የተሞላ ቢሆን እንኳን አኔ ግን አንድ ስንዝር ግንብ መገንባት ካልቻልኩ ትልቁ ታሪኬ መሀንዲስ መሆን ሳይሆን መሃንዲስ አለመሆን ነው፡፡ ሰው በምድራዊም ሆነ በፈጣሪ ህግ ፅድቅም ይሁን ኩነኔ የሚገጥመው በሰራው ስራ ወይም በግለሰብ ታሪኩ ነው፡፡
በታሪክ አረዳድ የግለሰብ ታሪክና ማንነት ያለውን ግዙፍ ድርሻ መረዳት በተወሰነ ደረጃ በታሪክ ዙሪያ ያሉብንን ግጭቶችና ጭቅጭቆች ሊያቃልልን ይችላል፡፡ የአገር እና የማህበረሰብ ታሪክ ላይ ብቻ የሚያጠነጥን አረዳድ የሰውን ልጅ ገፀ-ብዙ ያለው ማንነት ስለማይረዳ ግለሰብን የቡድን ማንነት ባሪያ ሊያደርገው ይችላል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ አንድ እጅጉን የተጨቆነ ማንነት የግለሰብ ማንነት ነው፡፡ ሰው በሁለት እግሩ ቁሞ ከቡድን አስተሳሰብ ባሻገር ግለሰባዊ ታሪኩን አጉልቶ ማህበራዊ ታሪኩን አክብሮ ሚዛኑን የጠበቀ አስተሳሰብ ሊይዝ የገባዋል፡፡ በአገር እና በማህበረሰብ ደረጃ ያሉ ብዙ ኩራቶቻችን በስተጀርባ የግለሰቦች ሚና ትልቅ ስፍራ ይይዛል፡፡ እንደውም እያንዳንዱ ሰው እንደ ሉዓላዊ አገር ታሪኩ ሊተረክለት የሚችል “አገር ወይም ብሔር” ነው።
አሁን ላይ ዓለምን ያንቀጠቀጠ ሥልጣኔ ያመጡት ምዕራባዊያን የግለሰብን ማንነትን ማጉላት እንደ አንድ የዕድገት መንገድ አድርgው ውጤታማ ሆነውበታል፡፡ የግለሰብ ማንነት በተገቢው መጠን ሲጎላ ሰዎች የቡድንን ማንነትን በማጦዝ የፈሪ ምሽግ ከማድረግ ይልቅ ግለሰባዊ አላፊነትን ወስደው ታሪክን ለመቀየር (ከግለሰብ ታሪካቸው ጀምረው) ይጥራሉ። በሰለጠነው ዓለም ያለውን ባህል ላየ ሰው አንድ ግልፅ የሚሆንለት ነገር የግለሰቦች የራሳችው ማንነትና ታሪክ ላይ ትኩረት ያደርገ የህይወት ዘይቤ ነው። ይህም እራስን በእውቀት እና በሃብት ለማበልፀግ ባላቸው ትጋት ይገለፃል። የዚህም ትጋታቸው ድምር ውጤት አገራቸውን በብልፅግና ይዟት ከፍ ይላል። በእርግጥ ከልክ ያለፈ የግለሰብ ማንነት የራሱ ችግር ሊያመጣ ይችላል የማህበራዊ ማንነትን ካለልክ ከተጋፋ።
ስንጠቀልለው በታሪክ ስንኮራ እንደ ግለሰብ ምን አይነት ሰው ነኝ ምን ሳደርግ ቆየሁ ወደ ፊትስ ምን አደርጋለው የሚለውን ያህል ታሪክ እኛን የሚወክል ታሪክ አለመኖሩን ማስታወስ ይገባል፡፡
ማጠቃለያ
ታሪክ በአግባቡ በባለሙያ ተተርኮ የጊዜ እና የግለሰብን ሚዛን ጠብቆ ከቀረበ ወደ ፊት ለሚመጣው ረጅሙ ታሪካችን ለመዘጋጀት ይረዳናል፡፡ ታሪክ የትላንት ብቻ አይደለም ታሪክ የነገም ነው፡፡ ታሪክ ያለፈ ብቻ አይደለም በእጃችን ያለ እና እንደመረጥነው የምንጽፈውም ነው፡፡ ታሪክ የአገር ወይም የማህበረሰብ ብቻ አይደለም የግለሰብም እንጂ። ዋናው ታሪካችን እንደውም የግለሰብ ታሪካችን ነው፡፡
በተሻለ የትላንት ታሪክ አረዳድ ላይ ተመርኩዘን የተሻለ የነገን ታሪክ እንድንገነባ ምኞቴ ነው።
ቸር ያቆየን