የተለመዱ ባህርያዊ ጉድለቶችና ዉሳኔዎቻችን
ለረጂም ግዜ፣ የምጣኔ ሃብት ባለሞያዎች ሰዉን የተረዱት እጅግ በጣም እራስ ወዳድ የሆነ ፍጥረት እንደሆነና የሚወስናቸዉ ዉሳኔዎች ሁሉ የራሱን ጥቅምና እርካታ በሚያረጋግጡለት መልኩ የመወሰን አቅም እንዳለውአድርገዉ ነበር። ይህም ማለት ዉሳኔዎቻችንን ላይ የምንደርሰው ያሉ አማራጮችን በሙሉ መዝነን የሚበልጥ ጠቃሚ የሆነውን የመምረጥ አቅማችንን ተጠቅመን ነው ብለው ያምኑ ነበር። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን እውነታው ከዚህ ራቅ ያለ እንደሆነ የሚያሳዩ ጥናቶች እየተበራከቱ በመምጣታቸው ባህርያዊ ምጣኔ ሃብት (Behavioural Economics) የሚባል የትምህርት መስክ ተፈጥሯል። ባህርያዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፦ 1) ሰዎች ሁሌም እራስ ወዳድ አደሉም (ለሌሎች ደም፣ ኩላሊት፣ ገንዘብ ወ.ዘ.ተ. ይለግሳሉ)፤ 2) ዉሳኔ ላይ ከመድረሳቸዉ በፊት ያሉዋቸዉን አማራጮች ሁሉ አይገመግሙም (ሲጀምር ስላሉት አማራጮች ሁሉም አይነት መረጃ ሊኖራቸው አይችልም፣ ቢኖራቸዉ እንኳ እያንዳንዳቸዉን ለመመዘን የሚያስችል የጭንቅላት (የማስላት) አቅሙም ግዜዉም አይኖራቸዉም)
በዚህ ምክንያት ታድያ፣ ሰዎች የሚወስኗቸዉ ዉሳኔዎች በሙሉ የራሳቸዉን ጥቅምና እርካታ የሚያረጋግጡ ናቸው ተብሎ መታመን አይቻልም ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ገንዘብ መቆጠብ እንዳለበት እያወቀ ግን መፈጸም ሲከብደው ይታያል፣ ሲጋራ ማጨስ ለጤና ጥሩ እንዳልሆነ እያወቀ ያጨሳል፣ ጓደኛዉን ላለማስቀየም አንድ ሁለት መለክያ መጠጥ ይጨምራል፣ ከአለቃው ጋር መጣላት ስራውን እንደሚጎዳው እያወቀ ይጣላል፣ ጎረምሶች ሲደባደቡ ካየ ገብቶ ይገላግላል፣ ወ.ዘ.ተ።
እነዚህን አይነት ሁኔታዎችን ተከትሎ፣ የምርምር ባለሞያዎች የተለያዩ ባህርያዊ ጉድለቶችን ለመረዳት ብዙ ምርምር በማድረግ ላይ ይገኛሉ። እኔም ይህ የምርምር ጥረት የለያቸዉን ባህርያዊ ጉድለቶች ምንነት እና ዉሳኔዎቻችን ላይ ስለሚኖራቸዉ ሚና በዚህና በተወሰኑ ተከታይ ጽሁፎች ለማቅረብ እሞክራለው።
1. የማረጋገጫ አድልዎ (confirmation bias)
መስማት የምንፈልገዉን እንሰማለን፤ ማመን የምንፈልገዉን እናምናለን
ባጭሩ፣ የማረጋገጫ አድልዎ ማለት፣ አንዴ የሆነ እምነት ከያዝን በዉሃላ፣ የምንፈሊጋቸዉ መረጃዎችም ሆኑ ያገኘናቸዉን መረጃዎች የምንተረጉመዉ/የምንረዳው ይሄንኑ እምነታችንን በሚያጠናክሩበት መንገድ ብቻ ሲሆን ማለት ነው። ይህም የሚሆንበት ምክንያት፣ በመጀመርያም የያዝነው እምነት ትክክል ነበር የሚል ማረጋገጫ ማግኘት ስለሚያስደስተን ነው።
ለምሳሌ፦ አዲስ መስርያ ቤት ስራ እንደተቀጠርን አከባቢ አንድ የስራ ባልደረባችን አልወደደኝም ብለን እንድናስብ የሚያደርገን መረጃ አገኘን እንበል። ይህ ሰው ምናልባትም በዛ ሰሞን ከባለቤቱ ጋር አለመስማማት ገጥሞት ስለነበር እንደሌሎቹ አዲሶቹ ባልደረቦቻችን ደማቅ ሰላምታ ስላልሰጠን ሊሆን ይችላል። አንዴ ይህን አይነት እምነት ካደረብን በኋላ ታድያ ከዚህ ሰው ጋር በሚኖሩን ግኙነቶች ሁሉ የምናገኛቸዉን መረጃዎች የምንተነትናቸው/የምንረዳቸው ያ ሰው ለኛ ካለው መጥፎ ስሜት የመነጩ እንደሆነ አድርገን ነው የሚሆነው ማለት ነው።
ተመሳሳይ የማረጋገጫ አድልዎዎችን በሃይማኖት፣ በፖለቲካና በመሳሰሉት ሁነቶች ዉስጥ ማግኘት ይቻላል።አንድ የሆነ ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ግለሰብ የሚሰበስበው መረጃ ከራሱ ሃይማኖት የሚመነጩ እና የሱን ሃይማኖት ትክክለኛነት የሚደግፉትን እየመረጠ የመሆን እድሉ እጅግ ከፍተኛ ነው። እንደዉ ስለሌላው ሃይማኖት የሚያነቡትም ቢሆኑ የሚያነቡበት ምክንያት ያ ሃይማኖት እንዴት ስህተት እንደሆነ ለማሳየት ስለሚሆን የሚሰበስቧቸዉ እና የሚያተኩሩባቸው ነጥቦች ይሀንኑ እምነታቸዉን የሚያጠናክሩትን ብቻ ይሆናል ማለት ነው። ፖለቲካም እንደዚሁ ነው። የምንደግፈዉን የፖለቲካ አካል መልካምነቱን የሚያጎሉ መረጃዎችን እየመረጥን ስንሰማ፣ የምንጠላዉን ደሞ የምንጠላበትን ምክንያት እየሰበሰብን እንሰማለን ማለት ነው። ለምሳሌ ይህ ቆየት ያለ ጥናት የሞት ቅጣት ፍርድ በአንድ አገር ህግ ውስጥ መኖር ወንጀልን በመቀነስ ረገድ ጠቃሚ ነው የሚል እና ጠቃሚ አይደለም የሚሉ የጥናት ዉጤቶችን (መረጃዎችን) ለተወሰኑ የጥናታቸዉ ተሳታፊ ለሆኑ ሰዎች በማሳየት የመረጃዉን አሳማኝነት እንዲገመግሙ ያደርጋቸዋል (መረጃዉ የቀረበበት መንገድ ታድያ በሁሉም ነገሩ ተመሳሳይ ሁኖ የሚለዉ ድምዳሜው ብቻ መሆኑን ልብ ይሏል)። ያገኘው ዉጤት የሚያሳየው ታድያ መጀመርያም የሞት ቅጣትን የሚደግፉ ግለሰቦች የሞት ቅጣት ወንጀልን ይቀንስዋል የሚለዉን መረጃ በጣም አሳማኝ እንደሆነ ሲገመግሙ፣ መጀመርያም የሞት ቅጣትን የሚቃወሙ ግለሰቦች ደግሞ የሞት ቅጣት ወንጀልን አይቀንስም የሚለዉን መረጃ በጣም አሳማኝ እንደሆነ ገምግምው አገኛቸው። ሌላ የቅርብ ጥናት ደግሞ፣ ፖለቲከኞች ከእምነታቸው (ከአቋማቸው) የሚቃረን መረጃ ሲሰጣቸው (አቋማቸውን) ይቀይራሉ አይቀይሩም የሚለዉን ለማጥናት የመንግስት ትምህርት ቤትን በተመለከተ (ትምህርትን መንግስት በነጻ ይስጥ፣ አይ የግሉ ዘርፍ ይስጥ በሚለው ክርክር ዉስጥ ያሉ) ደጋፊ እና ተቃዋሚዎች ፖለቲከኞችን የትምህርት ቤቶችን ዉጤታማነት የሚያሳይ መረጃ ከሰጧቸው በኋላ ፣ የመንግስት ነው የግል ትምህርት ቤት የተሻለው ብለዉ ሲጠይቋቸው፣ መረጃዉ ከእምነታቸው ጋር የሚስተካከል በሆነበት ጊዜ ብቻ ነው ፖለቲከኞቹ በትክክል የተሰጣቸዉን መረጃ የሚያስታዉሱት!
መረጃዎችን የራሳችንን የቀደመ እምነት በሚያጠናክሩበት ሁኔታ ብቻ በመተርጎምና በመረዳት ታድያ በራሳችን ምርጫ እና በያዝነው እምነት ትክክለኛነት ኩራት እና ደስታ እንቃርማለን ማለት ነው። በምርጫችን እስከተደሰትን ድረስ ታድያ የዚህ ችግር ምንድነው ልንል እንችላለን። ትልቁ ችግር እውነትን የማግኘት እድላችንን ያጠበዋል። እዉነትን ማግኘት የምንችለው (ቢያንስ ለእውነቱ የቀረበ አረዳድ ሊኖረን የሚችለው) ከራሳችን ስሜት ወጥተን ማንኛዉንም መረጃ (የሚደግፈንንም የሚቃረነንም) በመረጃነት ወስደን ማብላላት ስንችል ብቻ ነው። ካልሆነ ግን የተዛባን ወይም ያጋደለን እውነት እንደ እውነታ ወስደን የተንጋደዱ እና ጎጂ የሆኑ ዉሳኔውችን እየወሰንን እራሳችንን እየጎዳን ልንኖር እንችላለን ማለት ነው።
2. የባለቤትነት (የምክንያት/ የመንሰኤ) ማድላት (attribution bias):
ተሳካልኝ፦ ጠንክሬ ሰርቻለው በጣም ጎበዝ ነኝ ማለት ነው። አልተሳካልኝም፦ሁኔታዎች ስላልተገጣጠሙልኝ እኮ ነው፤እነእከሌ እኮ እንዲህ እንዲህ ስለአደረጉኝ እኮ ነው።
ይህ አድልዎ የሚመለከተው፣ ምክንያት እና ዉጤት በምናገናኘበት ጊዜ፣ ለመልካም ውጤቶች እራሳችንን እንደምክንያት ስናይ፣ ለመጥፎ ውጤቶች ደግሞ ከእኛ ዉጪ ያሉ ሁይሎችን ተጠያቂ የምናደርግበትን ባህርያዊ ጉድለት ነው። ለምሳሌ ይህ ጥናት ግለሰቦችን በእጣ ግማሾቹን ከባድ ስራ ሲሰጧቸው ለግማሾቹ ደግሞ ቀላል ስራ ይሰጧቸዋል ነገር ግን ምንም እንኳን ለተሳታፊዎቹ ከባድ እና ቀላል የሚባል ስራ እንዳለ ቢነገራቸዉም፣ እነሱ የተመደቡት የትኛዉ ላይ እንደሆነ ግን አልተነገራቸውም። ከዛ ያው ከባድ ስራ ላይ የተመደቡት በጣም ስኬታማ አልሆኑም ቀላል ላይ የተመደቡት ግን ስኬታማ በሆነ ሁኔታ ስራዉን መስራት ቻሉ። ከዛ የስኬታቸውን ምክኛት እንዲገልጹ ሲጠየቁ ታድያ፣ አብዛኞቹ ቀላሉ ስራ ላይ የተመደቡት ግለሰቦች የእራሳቸዉን ጥረት እንደምክንያት ሲያቀርቡ፣ ከባዱ ስራ ላይ የተመደቡት ግን እንደምክንያት ያቀረቡት የእድል ጉዳይ እንደሆነ አድርገው ነበር። ይህም የሆነበት ምክንያት አንዱ ለስኬታችን እራሳችንን በማሞገስ በእራሳችን ደስ ለመሰኘት እና በዉድቀታችን ደግሞ እራሳችንን በመዉቀስ ላለመደበት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ እራሳችንን እንደምክንያት ለማየት የሚቀናን የጠበቅነውን ዉጤት (ስኬት) ስናገኝ እንጂ ያልጠበቅነው (ዉድቀት) ሲገጥመን ስላልሆነ ነው (ያው ሰው ዉድቀትን አቅዶ አይንቀሳቀስም ከሚል ግምት ማለት ነው)። ይህ በሌላ አገላለጽ እራስን የማገልገል አድልዎ (self-serving bias) ተብሎም ይታወቃል። በዚህ ጉዳይ ላይ በጥልቀት ማንበብ ከፈለጉ፣ ይህንን ጥናት ይመልከቱ።
ነገር ግን፣ የባለቤትነት (የምክንያት/ የመንሰኤ) ማድላት ከራስችን ዉጪ ባሉ ሰዎችና ሁኔታዎችም ላይ ይኖረናል። ይህም ‘መሰረታዊ የባለቤትነት (የምክንያት/ የመንሰኤ) ማድላት’ (fundamental attribution bias) ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን የሌሎች ሰዎችን የህይወት ዉጤቶችንና የሁኔታዎችን አኳኳን በመመልከት ባለቤት ለመመደብ ስንሞክር የምንሳሳተው ነው። ለምሳሌ፦ ትዳሩ የፈረሰን ሰው ስናገኝ ምክንያት ለመስጠት እንሞክራለን። የምንሰጠዉ ምክንያት አወንታዊነት ወይም አሉታዊነት ታዲያ ለሰዉየዉ ካለን ስሜት ጋር ይቆራኛል። ለሰዉየው አዎንታዊ ስሜት ከሆነ ያለን፣ ትዳሩ የፈረሰው እኮ በሚስቱ ጥፋት ነው ልንል ስንችል አሉታዊ ስሜት ላለን ሰዉ ከሆነ ደግሞ ትዳሩ የፈረሰው እኮ ጸባይ ስለሌለዉ ነው ልንል እንችላለን ማለት ነው (እውነታው ግን ከሁለቱም ዉጪ ሊሆን ይችላል)።
ተመሳሳይ አድልዎ በቡድናዊ ህይወታችንም ዉስጥ አለ። ይህም የቡድን የባለቤትነት (የምክንያት/ የመንሰኤ) ማድላት (group attribution bias) በመባል ይታወቃል። እዚህም ላይ በተመሳሳይ፣ ከኛ ቡድን የሆኑ ሰዎችን ዉሳኔዎቻቸውንና ዉጤቶቻቸውን አዎንታዊ የሆነ ምክንያት ስንሰጣቸው፣ ከሌላ ቡድን ለሆኑት ደግሞ፣ ለተመሳሳይ ዉሳኔዎችና ዉጤቶች አሉታዊ የሆኑ ምክንያቶችን እንለጥፍባቸዋለን ማለት ነው። ለምሳሌ፦ እኛ የምንደግፈዉ ፖለቲከኛ ሲዋሽ፣ “ስትራቴጂ” ነው ብለን የምናልፈዉን ነገር የምንቃወመው ፖለቲከኛ ሲያደርገው ግን እንደዛ አይነት ሽፋን አንሰጠዉም ማለት ነው።
ታድያ የዚህ አድልዎ ችግር ምንድነው? በመጀመርያ፣ ለውድቀቶቻችን ከራሳችን ዉጪ ያሉ ሃይሎችን ብቻ ተጠያቂ የምናደርግ ከሆነ፣ ከስህተታችን ተምረን እንዳናድግ እንሆናለን ምክንያቱም እራሳችንን እንጂ ከኛ ዉጪ ያሉ ነገሮችን መቆጣጠር እንደማንችል ስለምናዉቅ። በተጨማሪም፣ በቀላሉ የአእምሮ እጥበት (brain-washing) ተጠቂ ልንሆን እና የቡድን መሪዎች አገልጋይ ልንሆን እንችላለን።
በቀጣይ፣ ሌሎች ባህርያዊ ጉድለቶችን ይዤ እመለሳለሁ። እስከዛዉ፣ ከባህርያዊ ጉድለቶች የተከለለ ቆይታ ተመኘሁ!
መረጃው ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
አመሰግናለሁ!