ደን እና መንግስት በኢትዮጵያ

(ክፍል 2)

የደኑ ዘርፍና የተጋነኑ አሃዛዊ መረጃዎች

በመጀመሪያ እንደአንድ በደኑ ዘርፍ እንዳለ ባለሞያ ባሁኑ ወቅት በመንግስት እየተመራ ባለው የዛፍ ችግኝ ተከላ ንቅናቄ ደስተኛ ነኝ። ነገር ግን በየዓመቱ ተተከሉ ተብለው ሪፖርት የሚደረጉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች እንዲሁም በተከላው ምክንያት መጡ የሚባሉ  ውጤቶች የተጋነኑ ናቸው የሚል አስተያዬት አለኝ። ምልከታዬን እንደሚከተለው ላስረዳ።

በመጀመሪያው የዘመቻ ዓመት (2019 ክረምት) 4 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ቻልን ተባለ። ይህን ቁጥር ለ 100 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ብናካፍለው እያንዳንዱ ሰው 40 ችግኞችን መትከል ነበረበት ማለት ነው። እንደሚታወቀው 100 ሚሊዮኑም ሰው ሁሉ ችግኝ ሊተክል አይችልም። ማለትም አጠቃላዩ የህዝብ ብዛት መትከል የማይችሉ ህፃናትን፣ አዛውንትን፣ ወዘተ ያካትታል። በእንደዚህ ዓይነት ዘመቻዎች የተለመደው አሰራር በቤተሰብ (at household level) አንድ ሰው ማሳተፍ ነው። በኢትዮጵያ አማካይ የቤተሰብ አባላት ብዛት 4.6 ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ቢያንስ የ 4 ቤተሰብ አባላቱን ድርሻ መትከል አለበት ማለት ነው። ይህም ማለት በዚያ ክረምት 4 ቢሊዮን ችግኞች ይተከሉ ዘንድ አንድ በዘመቻ የሳተፈ ሰው 160 ችግኞችን መትከል ነበረበት። ይህንን ማድረግ ተችሏል ወይ? በተለያዩ ምክንያቶች ይህ ተሳክቷል የሚል ግምት የለኝም። አንደኛ፣ ከሃገሪቱ ጫፍ እስከጫፍ ሁሉም ቤተሰቦች (households) ተሳትፈዋል ማለት አይቻልም። ሁለተኛ፣ ተሳተፉ የምንላቸው ግለሰቦች እንኳ በአንድ ወይም ሁለት የዘመቻ ቀናት ቢበዛ ከ 20 – 30 ችግኞች ቢተክሉ ነው። ሶስተኛ፣ እኔ እንደ ደን ሳይንስ መምህርነቴ ተማሪዎቼን በየጊዜው በነዚህ የተከላ ዘመቻዎች ተሳትፈው እንደሆነ እጠይቃለሁ። እና አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡኝ ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ (ከአንድ ክፍል ቢበዛ 10 የሚሆን) ነው። በተለያየ አጋጣሚ ከሰዎች ጋር ባለኝ ኢመደበኛ ውይይትም ይህንኑ ጥያቄ ሳነሳ በማገኘው ምላሽ ተክለናል የሚሉ ሰዎች ቁጥር አልተከልንም ከሚሉት ጋር ሲነፃፀር በጣም ትንሽ ነው። እናም 4 ቢሊዮን ችግኞቹን ማን ተክሏቸው ነው የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ይጋብዛል።

አሁን ደግሞ በዚህ ዓመት (2021) በጎረቤት አገራት ጭምር የሚተከሉ 6 ቢሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል የሚለውን አሃዝ ወስደን ከሌላ አቅጣጫ እንመርምረው። ችግኞችን ለተከላ የምናዘጋጅው በችግኝ ጣቢያዎች (tree nurseries) እንደሆነ ይታወቃል። ሃገራችን በአንድ ዓመት 6 ቢሊዮን ችግኞችን ማሳደግ የሚችሉ ችግኝ ጣቢያዎች አሏት ወይ? ኢትዮጵያ ውስጥ ስንት የዛፍ ችግኝ ጣቢያዎች አሉ? በትክክል ይህን ያክል ነው የሚል ቁጥር ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን በሥራ ምክንያት ወደ ወረዳ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮዎች የመሄድ አጋጣሚውን ካገኛችሁ በአንድ ወረዳ ከ 1 – 2፣ ቢበዛ 3፣  የችግኝ ጣቢያዎች ብቻ እንደሚገኙ ታውቃላችሁ። በኢትዮጵያ 670 ያህል የገጠር ወረዳዎችና 100 የከተማ ወረዳዎች አሉ። በእያንዳንዱ ወረዳ በአማካይ 2 ችግኝ ጣቢያዎች እንኳን ይኖራሉ ብንል (የከተማዎቹንም ጨምረንና በአየር ንብረት ምክንያት ችግኝ ጣቢያ ሊኖራቸው የማይችል የቆላ/በረሃማ አካባቢዎችን ግምት ውስጥ ሳናስገባ) በሃገሪቱ ባጠቃላይ ሊኖሩ የሚችሉት 770 × 2 = 1540 ችግኝ ጣቢያዎች ናቸው። በነዚህ ችግኝ ጣቢያዎች ስንት ችግኞችን ማምረት ይቻላል? የአንድ ችግኝ ጣቢያ የማምረት አቅም እንደ ትልቅነትና ትንሽነቱ (size) ፣ እንዳሉት መሰረተልማቶች (nursery infrastructure) ፣ እና የግባቶች መሟላት (seed, labor, containers/pots, potting media, etc) ይወሰናል። አብዛኞቹ የሃገራችን ችግኝ ጣቢያዎች በመጠናቸው ትንሽ የሚባሉ ዓይነት ናቸው። እንደው አንድ ችግኝ ጣቢያ በአማካይ 1 ሚሊዮን ችግኞች ያመርታል እንበል (1 ሚሊዮን ችግኞች ለማምረት ከ 400 በላይ ባለ 10 ስኩዬር ሜትር የችግኝ መደቦች ያስፈልጋሉ፣ እና ትንሽ ግምት አይደለም)። ይህን ስል ሁሉም ችግኝ ጣቢያዎች በሙሉ አቅማቸው ቢያመርቱ ብዬ ነው። ነገር ግን መሬት ላይ እንዲህ ሊሆን እንደማይችል ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን ። ለምሳሌ በዚህ ዓመት በብዙ ያገራችን ክፍሎች ካሉ አለመረጋጋቶች አንፃር ብዙ ችግኝ ጣቢያዎች በሙሉ አቅማቸው ይቅርና ምንም ችግኝ ላያመርቱ ይችላሉ። የሆነው ሆኖ በተነሳንበት ስሌት መሰረት ከ 1, 540 ችግኝ ጣቢያዎች ልናገኘው የምንችለው ከፍተኛ የችግኝ መጠን 1, 540 × 1, 000, 000 = 1, 540, 000, 000 (1.54 ቢሊዮን ነው)። እናም 6 ቢሊዮን ችግኝችን ከየት ልናመጣ ነው ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል። በነገራችን ላይ ቢሊዮን ቴሌቪዥን ላይ ወጥቶ በአፍ የመጥራት ያህል ቀላል ቁጥር አይደለም። አንድ ሰው እስከ ቢሊዮን ልቁጠር ቢል እንኳን ከ 30 ዓመት በላይ ይፈጅበታል ።

አከራካሪው የደን ሽፋን (area of land covered by forest) በኢትዮጵያ

ሌላው ብዙ ጊዜ ክርክር የሚነሳበት የደን አሃዛዊ መረጃ ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት ምን ያህሉ በደን የተሸፈነ ነው የሚለው ነው። ይህ አሃዝ በቀጥታ በሃገሪቱ ካለው የደን ጭፍጭፋ (deforestation) እና መልሶ ማልማት (reforestation) ጋር  ስለሚያያዝ መንግስት የሚያወጣው ሪፖርት ጥርጣሬ እንዲያጭር ያደርገዋል። እንግዲህ ከአንድ ሃገር የቆዳ ስፋት ውስጥ ምን ያህሉ በደን የተሸፈነ ነው የሚለውን ለመመለስ መጀመሪያ ደን ማለት ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይኖርብናል። ደን ምንድን ነው ለሚለው ደግሞ ሁሉንም የሚያስማማ አንድ ወጥ የሆነ ትርጓሜ (definition) ማግኘት ያስቸግራል። Chazdon et al. (2016) “When is a forest a forest . . .” በሚል ርዕስ በዚህ ዙሪያ ያቀረቡትን ትንታኔ ብንመለከት የደን ትርጓሜ እንደምንጠቀምበት ዓላማና እንደሚያወጣው ድርጅት የተለያየ ሆኖ እናገኘዋለን። ስለዚህ የሆነ አገር የደን ሽፋን ይህንን ያክል ፐርሰንት ነው የሚል ሪፖርት ስናገኝ የትኛውን የደን ትርጓሜ ተጠቅመው ነው ያሰሉት የሚለውን ማወቅ አለብን ማለት ነው።

በዚህ ረገድ ብዙ አገራት የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) በ የ5 ዓመቱ ለሚያወጣው ዓለም አቀፍ የደን ሃብት ዳሰሳ (Global Forest Resource Assessment) የሚጠቀምበትን የደን ትርጓሜ ይጠቀማሉ። ይኸውም፤

“Forest is land with tree crown cover (or equivalent stocking level) of more than 10% and area of more than 0.5 ha. The trees should be able to reach a minimum height of 5m at maturity in situ. May consist either of closed forest formations where trees of various storeys and undergrowth cover a high proportion of the ground; or open forest formations with a continuous vegetation cover in which tree crown cover exceeds 10%. Young natural stands and all plantations established for forestry purposes which have yet to reach a crown density of 10% or tree height of 5m are included under forest, as are areas normally forming part of the forest area which are temporarily unstocked as a result of human intervention or natural causes but which are expected to revert to forest.”

እንግዲህ በዚህ የFAO ትርጓሜ መሰረት የሆነ መሬት ደን ለመባል ግማሽ ሄክታር ቦታ መሸፈን፣ የቦታው 10% ያህል በዛፎቹ ቅርንጫፎች/ጥላ የተሸፈነ መሆንና ዛፎቹ ካደጉ በኋላ ቢያንስ 5 ሜትር ያህል ቁመት ካላቸው በቂ ነው። እንደወም ገና አዲስ የተተከሉ (ችግኞቹ ቢጸድቁም ባይጸድቁም) እና በተለያየ ምክያት ባዶ የሆኑ መርሬቶችን ሁሉ (ወደፊት በደን ይሸፈናሉ እስከተባለ ድረስ) ያጠቃልላል። ይህ የተለጠጠ ትርጓሜ ግን ደን ሲባል በብዙ ሰው አዕምሮ ውስጥ ከሚመጣው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ስዕል በእጅጉ የራቀ ነው።

ኢትዮጵያም ለFAO ሪፖርት ስታደርግ ይህንኑ የደን ትርጓሜ ስትጠቀም ቆይታለች። ከ 2018 ጀምሮ ግን ከዚህም በባሰ የተለጠጠና በተለምዶ ቁጥቋጦ (Scrubland/bushland) የሚባሉ ቦታዎችን የሚያካትት የራሷን የደን ትርጓሜ እየተጠቀመች ትገኛለች። ይኸውም፤

“Forest is land spanning at least 0.5 ha covered by trees and bamboo, attaining a height of at least 2m and a canopy cover of at least 20% or trees with the potential to reach these thresholds in situ in due course.”

ይህ እንደሚያሳየው በእኛ አገር ትርጓሜ ደን ለመባል ከላይ ያየነው የFAO መስፈርት እንዳለ ሆኖ የዛፎቹ ቁመት ግን እስከ 2 ሜትር (የአንድ ረጅም ሰው ቁመት ያክል) ሊያጥር ይችላል። እርግጥ ይህንን ትርጓሜ ለመጠቀም ገፊ የሆነው ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያግዝ የሃገሪቱ የደን ሃብት ዳሰሳ ሲደረግ በቆላማ አካባቢ(drylands) የሚገኙና በፊት እንደ scrubland ይቆጠሩ የነበሩ ቦታዎችን ለማካተትና የ REDD+ ድጋፍ ለማግኘት ሲባል ነው። ይህ በራሱ መልካም ሆኖ ሳለ፣ ችግር የሚሆነው ግን በዚህ መልኩ የደንን ትርጓሜ በመቀየር የመጣን የሃገሪቱ የደን ሽፋን ፐርሰንት እድገት (increase in percentage of land covered by forest) መንግስት በሠራቸው የደን ልማት ሥራዎች (afforestation and reforestation) እንደመጣ ተደርጎ ሪፖርት ሲደረግ ነው።

የቅርቡን የFAO ሪፖርት (FRA 2020) ስንመለከት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 15.7% ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ ቁጥር ከ 2005 – 2015 11% አካባቢ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የበለጠ ነው። ነገር ግን እዚያው የ2020 ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው ልዩነቱ የመጣው አዲስ የመረጃ ምንጭ (new data) እንዲሁም አዲሱን የደን ትርጓሜ (new definition) በመጠቀማቸው ነው። በዚህም የተነሳ በቀደሙት ሪፖርቶች እንደ scrubland/other wooded land  ይቆጠሩ የነበሩ ቦታዎች በአሁኑ በደን ውስጥ  እንዲካተቱ ተደርገዋል።

ስለዚህ በአንዳንድ የመንግስት ሪፖርቶች (በተለይም በመገናኛ ብዙሃን) “ተመናምኖ ከ3% በታች የነበረውን የደን ሽፋን ወደ አስራ ምናምን ፐርሰንት አሳድገናል” ተብሎ የሚገለጸው ትክክል አይደለም። በነገራችን ላይ የሃገሪቱን የደን ስፋት (በሄክታር) ካዬን አሁንም እየቀነሰ እንደሚገኝ ይሄው FAO 2020 ሪፖርት ላይ መመልከት ይቻላል። ከ1990 ጀምሮ በየ 5 ዓመቱ በተገለጸው መረጃ መሰረት የኢትዮጵያ በደን የተሸፈነ መሬት እድገቱ ሁሌም ከዜሮ በታች (negative) ነው። በ 1990 19, 258, 500 ሄክታር የነበረ ሲሆን እዬቀነሰ መጥቶ በ 2020 17, 068, 500 ሄክታር ሆኗል። ይህ የሚያሳየው ምንም እንኳን ቀደም ብዬ የጠቀስኳቸው አዳዲስ የተከላ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ቢሆንም፣ የደን ጭፍጨፋ (deforestation) ግን በበለጠ መጠን እየጨመረ መሆኑን ነው። የኢትዮጵያን የደን ጭፍጨፋ መጠን (rate of deforestation) የሚያሳዩ ሪፖርቶች በአንድ ወቅት (በ 1900ዎቹ መጀመሪያ) የሃገሪቱ የደን ሽፋን 40% እንደነበረና ከዚያ በተከታታይ ወርዶ፣ ወርዶ በ 2000 ከ 3% በታች እንደደረሰ ይጠቅሳሉ። ይህ አሃዝ የሚያመለክተው ግን ጥቅጥቅ ያሉ የተፈጥሮ ደኖችን (natural high forests) እንጂ ከላይ በተጠቀሱት የተለጠጡ የደን ትርጓሜዎች መሰረት ወደ ደን የሚካተቱ ቦታዎችን ሁሉ ማለት አይደለም። እንደ አንድ አስረጅ Reusing (2000) “Change detection of natural high forests in Ethiopia using remote sensing and GIS techniques” በሚል ርዕስ ያሳተመውን የምርምር ጽሑፍ ማዬት ይቻላል። ስለዚህ “የሃገሪቱን የደን ሽፋን ከወረደበት < 3% ከፍ አድርገነዋል”  የሚሉ ሪፖርቶች/ዘገባዎች በመሰረቱ ሀሰት ናቸው።

ማጠቃለያ

መንግስት በአሁኑ ወቅት ለደኑ ዘርፍ የሰጠው ትኩረትና በየዓመቱ ብዙ ችግኞችን ለመትከል የሚደረገው ንቅናቄ የሚመሰገን ነው። ሆኖም ግን በሚዲያ ከሚገለፁ ግዙፍ ቁጥሮች (ቢሊዮኖች) በዘለለ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በተገነዘበ መልኩ ቢሠራ መልካም ነው። የዛፍ ችግኝ ተከላው ከዘመቻ ሥራና ከሚዲያ ጋጋታ ተላቆ በሚመለከተው መሥሪያ ቤት ታቅዶና ክትትል እየተደረገበት ቢሠራ የበለጠ ውጤታማ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። ያኔ ከከተሞች ራቅ ያሉ፣ የባለስልጣናት መኪናና ቪድዮ ካሜራ የማይደርስባቸው የተራቆቱ ተራራማ የሃገሪቱ ክፍሎች መልሰው ደን የመልበስ እድል ይኖራቸዋል። በተጨማሪም ለአዳዲስ ችግኞች ተከላ ከሚሰጠው ትኩረት ባልተናነስ አሁንም በስፋት እየቀጠለ ያለውን የደን ጭፍጨፋ (deforestation) ለማስቆም/ለመቀነስና እየተመናመኑ መጥተው ለመጥፋት የተቃረቡትን የተፈጥሮ ደኖች ለመጠበቅ መሥራት ያስፈልጋል።

ጸሐፊውን  በ nigussub@yahoo.com ማግኘት ይቻላል።

Please share this to:

3 Replies to “ደን እና መንግስት በኢትዮጵያ”

  1. ያኔ ከከተሞች ራቅ ያሉ፣ የባለስልጣናት መኪናና ቪድዮ ካሜራ የማይደርስባቸው የተራቆቱ ተራራማ የሃገሪቱ ክፍሎች መልሰው ደን የመልበስ እድል ይኖራቸዋል። …..Nice, crucial, relevant and priceless recommendation…..keep it up please…

  2. Thank You! The government lies !!!!!! I don’t think Et has the potential (even peace and stability) to plant and protect 10 million tree a year. Billion trees are not easy, can also be visible from space. House of Card!!!

Comments are closed.

Social media & sharing icons powered by UltimatelySocial