የተለመዱ ባህርያዊ ጉድለቶችና (ዝንፈቶችና) ዉሳኔዎቻችን፦ ከባለፈው የቀጠለ
ከዚህ ቀደም ሁለት ባህርያዊ ጉድለቶችን (ዝንፈቶችን) አቅርቤላችሁ በቀጣይ ጽሑፍ ደግሞ ተጨማሪ የዝንፈት ዓይነቶች ይዤ ለመመለስ ቀጠሮ ነበርኝ (አዚህ ይመልከቱ)። የመጀመርያውን ክፍል አንብቦ ጉድለት ከሚባል፣ ዝንፈት ቢባል ይሻላል ብሎ ሃሳብ ለሰጠኝ አንባቢ ምስጋና እያቀረብኩ፣ ከዚህ በኋላ ባለው ፅሁፍ ላይ ዝንፈት የሚለዉን ቃል የምጠቀም መሆኔን አስቀድሜ ላሳዉቅ እወዳለሁ::
በዚህ ጦማር ላይ ሶስት ባህርያዊ ዝንፈቶችና በዉሳኔዎቻችን ላይ ስለሚኖራቸዉ ሚና አቀርባለሁ፡፡ እነዚህን ዝንፈቶች በተቻለኝ አቅም የአማርኛ አቻ ስያሜ እሰጣቸዋለሁ። አንደተለመደው ትርጉሙን በማሻሻል አንድትተባበሩኝ እጋብዛለሁ፡፡ ለዛሬ የማቀርባቸው ባህርያዊ ዝንፈቶች፦ ፩) Hindsight bias የኋልዮሽ እይታ ዝንፈት)፣ ፪) Anchoring bias (የመልህቅ ዝንፈት)፣ እና ፫) Framing effects (የክፈፍ ውጤቶች ናቸው)።
፩) Hindsight bias (የኋልዮሽ እይታ ዝንፈት)
እንደዚህ እንደሚሆን አዉቅ ነበር። ይህ እንደሚሆን ቀድሞዉን ታይቶኝ ነበር።
የኋልዮሽ እይታ ባህርያዊ ዝንፈት የሚከሰተው ሰዎች አንድ ነገር ከተከሰተ በኋላ፣ የተከሰተውን ነገር የተገማችነት እድል ከሆነው በላይ ከፍ ያለ እንደነበር ሲያምኑ ነው። እንደዚህ የምናስብበት ወይም የምናምንበት ምክንያቶች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው ተብሎ ይታመናል ፦ 1) ከተከሰተዉ ሁኔታ ጋር ተያይዞ፣ ከመከሰቱ በፊት የነበሩ መረጃዎችን አእምሮአችን ለማስታወስ ሲመርጥ፣ ለተከሰተዉ የቀረቡትን አጉልቶ ስለሚሆን፣ ዉጤቱን የተሻለ ገምተነው የነበርን እንዲመስለን ያደርገናል፤ 2) ሰዎች ባጠቃላይ ሁኔታዎችን አስቀድሞ የመተንበይ ብቃት አለን ብለን ማሰብ/ማመን ስለምንወድ ሲሆን፤ እንደዚህ በማሰባችን ታድያ በህይወታችን ላይ የተሻለ ቁጥጥር አለን ብለን ለማሰብ እና የአእምሮ ሰላም ለማግኘት ስለሚረዳን።
ይህ ነገሮች ከተከሰቱ በኋላ ቀድሞ ታይቶን/ታዉቆን ነበር ብለን ማመናችን ታድያ ለአላስፈላጊ መተቻቸት ልናዉለዉ እንችላለን። ለምሳሌ፦ የጓደኛችን ባለቤት ማገጠ/ች የሚል መረጃ ብናገኝ “እሱ/እሷ እንዴት እንዳልታያት እንጂ፣ እኔ ገና ድሮውንም ሳየው/ሳያት አርፎ የማይቀመጥ/የማትቀመጥ እንደሆነች ታውቆኝ ነበር” ልንል እንችላለን። እዚህ ላይ ማስታወስ ያለብን ግን፣ ስለአለፈው አረዳዳችን ትክክለኛነት ላይ እርግጠኛ ሁነን የምንሞግተው አሁን ላይ ስለክስተቱ በቂ መረጃ ከያዝን በኋላ መሆኑን ልብ እንበል። ሌላም ብዙ ምሳሌዎችን ማንሳት እንችላለን። ጓደኛችን ስኬታማ ሲሆን፦ እኔ ድሮም አዎቅ ነበር አንተ ጥሩ ቦታ እንደምትደርስ፤ ሀኪሞች የምርመራ ዉጤት ካዩ በኋላ፦ ድሮም በሽታዉ ይህ አንደሆነ ገምቼ ነበር፤ ከመኪና አደጋ ለትንሽ ስንተርፍ፦ ድሮም የሆነ ነገር ሲቀፈኝ ነበር የዋለው ስንል ማየት በጣም የተለመደ ነው:: ምን ያክሉ በትክክል አስቀድመን ያሰብነው እንደሆነ፥ ምን ያክሉ ደግሞ ዉጤቱን አይተን ስናበቃ ባገኘነው መረጃ ላይ ተመርኩዘን የፈጠርነው አምነት እንደሆነ ማወቅ ከባድ ስለሆነ ሁሌም እራሳችን ላይ ጠንካራ እምነት ይዘን ስናገኘው የተወሰነ መጠርጠር ግን ጥሩ ነው:: (በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ለማውቅ ይህን እና ይህን ጥናት ይመልከቱ)።
፪) Anchoring bias (የመልህቅ ዝንፈት)
የመልህቅ ዝንፈት ማለት ከዉሳኔያችን በፊት ያየናቸው ወይም የሰማናቸው ነገርግን ተዛማጅነት የሌላቸው መረጃዎችበቀጣይ ውሳኔዎቻችን ወይም አመለካከታችን ላይ ተጽእኖ የሚያሳድርበትን ክስተት ይወክላል። ይህ የሚሆነውአእምሮአችን ያገኘውን የመጀመርያ መረጃ ቀጥለዉ ለሚመጡ ሁነቶች ወሳኝነት አለው ብሎ ስለሚቀበል ሲሆንበብዛት የሚስተዋለው ደግሞ ቁጥር-ነክ የሆኑ ዉሳኔውች ላይ ነው::
ለምሳሌ:- የኖቤል ተሸላሚው ዳንኤል ካህንማን አና አሞስ ትቨርስኪ የሰሩት አንድ ጥናት ሰዎችን ለሁለት ቡድን ከፍለው ግማሾቹን ‘spinning wheel’ አሽከርክረው አነስተኛ ቁጥር (10 ቁጥርን) እንድያዩ አደረጉ፤ የቀሩትን ግማሾች ደግሞ ትልቅ ቁጥር (65 ቁጥርን) አንድያዩ አደረጉ:: ከዛ ለሁለቱም ቡድን የሚከተለዉን ጥያቄ አቀረቡላቸው:- በየተባበሩት መንግሥታት ዉስጥ ካሉ ሃገራት ዉስጥ የአፍሪካ ሃገራት ስንት በመቶ ይሆናሉ? የመጀመርያዎቹ ትንሽ ቁጥር ያዩት ቡድን አባላት ባማካኝ 25 በመቶ ሲሉ፤ የተቀሩት ደግሞ 45 በመቶ አሉ:: ይህ የሚያሳየው፦ ምንም እንኩን መጀመሪያ ላይ ያዩት ቁጥር የተባበሩት መንግሥታት ዉስጥ ካሉ የአፍሪካ ሃገራት ቁጥር ጋር ምንም ግንኙነት ባይኖረዉም፤ መጀመሪያ አነስተኛ ቁጥር እንድያዩ የተደረጉት አነስተኛ ግምት ሲያስቀምጡ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያዩት ደግሞ ከፍተኛ ግምት አስቀምጠው ተገኝተዋል::
ሌሎችም በርከት ያሉ ጥናቶች የዚህን የባህርይ ዝንፈት መኖር አና በህይወታችን ላይ ስላለው ምልክታ አስነብበዋል:: ለምሳሌ፦ ዳን አርያሊ እና ባልደረቦቹ የሰሩት አንድ ጥናት አንደሚያሳየው ከሆነ የጥናት ተሳታፊዎችን የተለያዩ እቃዎችን (እንደ ቸኮሌት ወይን ያሉ) ለመግዛት መጀመርያ የተሳታፊዎችን የማህበራዊ ዋስትና (social security) የመጨረሻ ሁለት ቁጥሮችን አንደመነሻ ዋጋ አድርጎ እቃዉን በዛ ዋጋ ለመግዛት ያላቸዉን ፍላጎት ይጠይቃቸዋል (ማለትም የመጨረሻ ቁጥሮች 1 እና 5 ከሆነ በ 15 ዶላር ሊገዙ 9 እና 8 ከሆነ ደሞ በ 98 ዶላር ሊገዙ ማለት ነው):: ከዛ በመቀጠል እራሳቸዉ በትክክል ዕቃዎቹን ለመግዛት ፈቃደኛ የሆኑበትን ዋጋ ለጨረታ እንድያስገቡ ይጠይቃቸዋል:: ታድያ የማህበራዊ ዋስትና የመጨረሻ ሁለት ቁጥራቸው ከአማካኙ ይተልቅ የነበሩ ተሳታፌዎች ባማካይ ትልቅ ዋጋ ለመክፈል ሲስማሙ የማህበራዊ ዋስትና የመጨረሻ ሁለት ቁጥራቸው ከአማካኙ ያንስ የነበሩት ደግሞ ያነሰ ዋጋ ለመክፈል አስገብተው ተገኙ:: በመጨረሻም፦ የማህበራዊ ዋስትና ቁጥራቸው ላይ ተንተርሶ የተጠየቁት ዋጋ ለጨረታ ያስገቡት ዋጋ ላይ ተጽኖ ነበረው ወይ ተብለው ሲጠየቁ፣ አብዛኞቹ (72 በመቶ) የሚሆኑት አልነበረዉም ብለው መለሱ::
ይህ ማለት የመልህቅ ባህራዊ ዝንፈት የተለያዩ ግብይቶችን በምናደርግበት ወቅት ዳፋ ሊኖረው ይችላለ:: ለምሳሌ፦ አልጋ ልንገዛ ወጥተን መጀመርያ ያየነው አልጋ ዋጋው 100,000 ብር ቢሆን፣ ሌላ አልጋ በ30,000 ብር ስናይ ይሄኛው በጣም ርካሽ መስሎ ሊታየን ይችላል:: ነገር ግን የመጀመሪያውን ዋጋ ሳናይ ቢሆን ፣ ሁለተኛዉን አልጋ ርካሽ ሆኖ ላይታየን ይችል ነበር:
፫) Framing effects (የክፈፍ ውጤቶች)
ይህ የባህርይ ዝንፈት ደግሞ የሚከሰተው የአንድ መረጃ ይዘት ሳይቀየር፣ ነገር ግን የቀረበበት መንገድ ብቻ ሲቀየር ዉሳኔያችንን በሚታይ መልኩ ሲቀይረው ነው:: ለምሳሌ፦ ተመሳሳይ የእጅ ማፅጃ ሳንታይዘር የሚያመርቱ ሁለት ፋብሪካዎች አሉ እንበል:: አንደኛው ላይ 90% ጀርም የሚገድል የሚል ተፃፎበታል፤ ሌላኛው ላይ ደግሞ 10% ጀርም ብቻ የማይገድል የሚል ተፃፎበታል፡፡ የቱን እንገዛለን? አብዛኞቻችን 90% ጀርም የሚገድል የሚለዉን ሳንታይዘር የመምረጥ እድላችን እጅግ ከፍ ያለ ነው:: እዚህ ላይ ልብ ብለን ካስተዋልንው ሁለቱም ፋብሪካዎች የሚያስተላልፉት መረጃ ከይዘት አንጻር አንድ አይነት ነው የቀረበበት መንገድ ቢለያይም:: አንደኛው መረጃዉን የሰጠን ከሳኒታይዘሩ ከምናኘኘው ጥቅም አንፃር ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከምናጣው ጥቅም አንፃር ነው::
እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ዉሳኔዎቻችን ላይ ተጽኖ የሚኖራቸው ደግሞ ሰዎች በተፈጥሮ ማግኘትን እና ማጣትን የምንመዝንበት ሚዛን ስለሚለያይ ሲሆን ለማጣት ከማግኘት የበለጠ ክብደት እንሰጠዋለን:: ይህም ማለት ተመሳሳይ እሴት/ዋጋ ያለው ነገር ቢሆንም በማግኘት ከምንደሰተው በላይ በማጣት የምንታመመው/የምናዝነው ይበልጣል:: ለምሳሌ፦ 100 ብር ወድቆ ስናገኝ የምንደሰተውን እና ወድቆ ሲጠፋብን የምናዝነዉን እናስብ:: ይህ ኩነት ‘Prospect Theory’ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ሃሳቡን በስፋት እንዲታውቅ ያደረጉት ደግሞ ዳንኤል ካህንማን አና አሞስ ትቨርስኪ ናቸው (ይህን ጥናታቸዉን ይመልከቱ)::
ጽሁፌን ከመቋጨቴ ብፊት ከላይ ከተጠቀሱት የባህርይ ዝንፈቶች እናንተና በዙሪያችሁ ያሉ ሰዎች በየትኞቹ ይበልጥ ተጠቂነን ብላችሁ ታስባላችሁ?
ሌሎችም በርካታ ዝንፈቶች እንዳሉ እያስታወስኩ እና እንድታነቡ እየጋበዝኩ፣ በዚህ ርዕስ የጀመርኩትን ጦማር አበቃሁ::