ነፅሮተ እውነት

የኢንተርኔት ዘመን ትልቅ እድል ይዞ መጥቷል፡፡ ይኸውም መረጃን በቀላሉ የማግኘት እድል ነው። ባለንበት ዘመን የመረጃ ጎርፍ ልክ እንደ ክረምት ጎርፍ አሰስ ገሰሱን እየጫነ ይመጣል፡፡ ታዲያ ልክ የጎርፍ ውሃ እንዳለ ለመጠጥነት እንደማይበቃው ሁሉ ይኸውም የመረጃ ጎርፍ ለጥቅምነት ከመዋሉ በፊት በጥንቃቄ ሊጠለል ግድ ይላል፡፡ አልያ ሐሰቱን ከእውነት ቀላቅሎ የመጣውን ጎርፍ እንዳለ ከተቀበልነው የአስተሳሰብ በሽታ ያስከትላል። በሽታውም የተዛባ አመለካከትን እና የተሳሳተ ግንዛቤን ፈጥሮ በተለያየ መንገድ ጉዳት ያደርስብናል፡፡

በዚህ ጽሁፍ እውነቱን ከሀሰት ለማጥለል የሚረዱ ጠቃሚ ነጥቦችንና ዘዴዎችን ለመጠቆም እሞክራለሁ፡፡   ይህ ጥቆማ ከጉዳዩ ስፋትና ጥልቀት አንጻር ከፊል ሽፋን ብቻ እንዳለው እያሳሰብኩ ወደ ዝርዝሩ እገባለሁ፡፡

ሀ) መልካምነትን ከተንታኝነት ማስቀደም

ምንም እንኳን ምክንያታዊ ትንታኔ  (አመክንዮ) እውነትን አንጥሮ ለማውጣት ሁነኛ መሳሪያ ቢሆንም ከሁሉ የሚቀድመው የእውቀት መሠረት ግን መልካምነት ነው፡፡ እዚህ ጋር መልካምነት የተባለው ግብረ ገብነት ሲሆን በህብረተሰቡ ዘንድ ምግባረ ቀና የሚያስብሉ ፀባዮች ያሉትን ሰው ያመለክታል። የመልካም ሰው ጠባያት ሊባሉ የሚችሉትም፦ ፍትሃዊነት ፣ ትህትና ፣ ሩህሩህነት ፣ ሰውን መውደድ፣ ወዘተ ናቸው፡፡

ሰው መልካም ስብህናን የተላበሰ ካልሆነ የፈለገ እውነትን ቢመረምር ሰንካካ ወደ ሆኑ አሳቦች ያደላ የተዛባ አረዳድ ላይ መውደቁ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ በሰው እኩልነት የማያምን ሰው ባንድ በኩል የራሱን ማንነት የሚያገዝፉ መረጃዎን አጽንኦት ሲሰጥ በተቃራኒው ደግሞ የሌሎችን ድክመት እየነቀሰ በእውነት ላይ  ያልተሰመረተ የራሱን አለም ፈጥሮ ይኖራል፡፡ ይህም ዓለም ራስን በንፅፅር ወደ ላይ ሰቅለው የሚኮፈሱበት የቅዠት ዓለም ነው። በስነ ልቦና ሳይንስም ሰዎች በልባቸው ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ የሚያጠናክሩ መረጃዎችን ብቻ ለይተው የማየት ዝንባሌ እንዳላቸው ተረጋግጧል፡፡ ሌላ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የትህትና እና እውነትን ዝምድና ማየት ነው። ትሁት የሆነ ሰው ሌሎች እኔ የማላውቀው ነገር ማወቃቸው አይቀርም ብሎ ስለሚያምን አእምሮውን ክፍት አርጎ የሌሎችን ሀሳብ በመስማት እውቀትን ያዳብራል። ትህትና የሌለው ግን ሁሉን አውቄአለው ብሎ ከመስማት መናገርን እያስቀደመ እውነትን በደንብ ሳያጣጥማት ይቀራል። 

ስለዚህ አንዱና ዋንኛው እውነትን የመለየት መሠረት መልካም ሰው መሆን ነው። ይህ መሰረት የሆነ ነገር ችግር ካለበት የንባብ ብዛትና የዲግሪ ጋጋታ ወደ እውነት ሊያደርስ አይችልም፡፡ አንዳንዴ እንዴት የተማሩ ሠዎች እንዲህ ይላሉ ወይም ያደርጋሉ ስንል ይህን ነጥብ ማስታወስ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡

ለ) ማንነትና እውነት

ዘር ከልጓም ይስባል የሚለው አባባል ይህን ርዕስ በደንብ ይገልጸዋል፡፡ ብዙ ሰዎች የማንነታቸው ጥገኛ ናቸው፡፡ የእኛን ሀገር ፖለቲካ ላስተዋለ የተሻለ ምሳሌ ማምጣት ይከብዳል፡፡ በሀገራችን ከሊቅ እስከ ደቂቁ የፖለቲካ አቋሙ ከብሔር ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በዚህ ስሜትን ሰቅዞ በሚይዝ የብሔርተኝነት ስሜት የተያዘ ሰው የሚያየው መረጃ ሁሉ የፖለቲካ አቋሙን ከማጠናከር ውጪ ሚዛናዊ ወደ ሆነ አመለካከት አይመራውም፡፡ በአንድ ሀገር ላይ የመናገር ነጻነት ቢኖርም ማንነት የማሰብን ነጻነት ከወሰደው ነገሩ ሁሉ ቢወቅጡት እንቦጭ ነው፡፡

ከዚህ ችግር የመውጫው ቀዳሚው መንገድ የችግሩን መኖርና ክብደት መረዳት ነው፡፡ ከዚያም ስራዬ ብሎ በዕለት ተዕለት ሀሳብና ውሎ ላይ ማንነቴ ተፅህኖ አድርጎብኝ ይሆን እንዴ ብሎ እየጠየቁ መኖር ይገባል። ባጭሩ ማንነት የእውነት ጠላት ሊሆን ይችላል። በክርስትያኖች መፅሀፍ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ ” የሚለው በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።

ከዚህ በተጓዳኝ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ ብዙ የመረጃ ምንጮቻችን የዚህ ችግር ሰለባ ሊሆኑ ስለሚችሉ የሚያቀርቡትን መረጃ በጥንቃቄ የመመርመር አስፈላጊነት ነው።ለምሳሌ የምህራብ ሚዲያዎች የምህራብ ማንነት ያላቸው ስለሆኑ በዚህ ምክንያት መረጃዎቻቸው ከችግር ነጻ የመሆናቸው እድል አናሳ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያንም ሚድያዎች በተመሳሳይ መንገድ መመርመር ይኖርባቸዋል።     

ሐ) በቂ ናሙና ወይም ተጨማሪ ማረጋገጫ

አንድ ሳንቲም 3 ጊዜ ቢወረወር ሶስቱንም ጊዜ ተመሳሳይ ገጽ የመምጣቱ ዕድል ከ4፣ 1 ነው ወይም 25% ነው። ሊታወቅ የሚፈለገው እውነት የሳንቲሙ ሁለት ገፆች ምን እንደሚመስሉ ከሆነ አንድ ሳንቲም 3 ጊዜ ሲወረወር አይተን ሳንቲሙ በሁለቱም ገጽ ተመሳሳይ ነው ብለን የተሳሳተ ድምዳሜ የመስጠት ዕድላችን 25%  ነው ማለት ነው፡፡ ሳንቲሙ ከ3 ጊዜ በላይ ጊዜ ከተወረወረ ግን የመሳሳት ዕድላችን እጅግ እየተቀነሰ ይመጣል፡፡ ለምሳሌ 5 ጊዜ ቢወረወር 5ቱም ተመሳሳይ የመሆናቸው እድል 6% ገደማ ነው። ይህ የሚያሳየው የናሙናችን መጠን ከፍ ባለ ቁጥር እውነቱን የመረዳታችን ዕድል እየሰፋ ይመጣል።

ከተላያዩ ምንጮች የምናገኘው መረጃም በበቂ ናሙና ላይ የተመሰረተ ካልሆነ ልክ እንደ ሳንቲሙ ለተሳሳተ ድምዳሜ የመዳረጋችን ዕድል የሰፋ ነው። ለምሳሌ አንድን ሰው ብቻ ቃለ ለመጠይቅ አድርጎ የሚዘግብ ጋዜጠኛን መረጃ አክብደን ማየት የለብንም፡፡ ወይንም እንድን የፌስቡክ መረጃ ይዘን ድምዳሜ ላይ መድረስ ልክ አንዴ ብቻ የተወረወረን ሳንቲም አይተን ሳንቲሙ በሁለቱም በኩል ጎፈር ነው ብሎ እንደመደምደም ሊቆጠር ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የሚወሰደው ናሙና በጥንቃቄ ወካይ ሆኖ መወሰድ ይኖርበታል። ጋዜጠኛው ብዙ ሰው ቃለመጠይቅ ቢያደርግም ሁሉም ሰዎች አንድ ላይ ሲያወሩ ያገኛቸው ከሆነ ሃሳባቸው ተመሳሳይና ልናጠና የፈለግነውን ማህበረሰብ የሚወክል ላይሆን ይችላል።

መረጃችን የሳይንሳዊ ጽሁፍ እንኳን ቢሆን በአንድ ወይም በጥቂት ጥናት ወረቀቶች ላይ መመስረት ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ ሊያደርስ ይችላል፡፡   በአንድ ጉዳይ ላይ 100 ጥናቶች   ቢደረጉ ሁሉም ተመሳሳይ ነገር አያሳዩም። ለምሳሌ 95ቱ ተመሳሳይ ውጤት ሲያሳዩ 5ቱ ግን ለየት ያለ ውጤት ሊያመለክቱ ይችላሉ፡፡ ታዲያ ጥቂት ጥናቶች ከሆነ ያየነው በአጋጣሚ ያየናቸው ሁሉም ከ5ቱ ወገን የመሆን እድላቸው የሰፋ ነው፡፡ ይህም በስፋት በመረጃ ከተደገፈው ግኝት ይልቅ አናሳ ድጋፍ ያለውን የመቀበል ስህተት ልንፈፅም እንችላለን።

መ) ሰበብን (cause) ከዝምድና (correlation) መለየት

አንድን ውጤት የሚያመጡ የተለያዩ ሰበቦች ወይም ገፊ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንድን ተክል ውሃ ማጠጣት ተክሉን ሊያሳድገው ይችላል፡፡ ውሃው እዚህ ላይ ሰበብ ሲሆን እድገቱ ደግሞ ውጤት ነው፡፡ ሆኖም አንዳንዴ ሰበብ የሚመስሉን ነገሮች አጋጣሚዎች እንጂ ከውጤቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የላቸውም፡፡   ለምሳሌ የአንድ ሀገር ዓመታዊ ምርት አዲስ መሪ ከተመረጠ በኋላ  ቢያሻቅብ  የምርቱን መጨመር  ከመሪው  ጋር  የማገናኘት  እድላችን  ሰፊ ነው፡፡  ነገር ግን  የምርት ዕድገቱ  ከመሪው ጋር  ምንም  አይነት ግንኙነት ላይኖረው  ይችላል፡፡ የምርቱ  መጨመር የሚገናኘው ከተለመደው መጠን ከፍ ካለ ዝናብ ጋር ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡   በዚህም አለም  የአንድ ውጤት ሰበቡ ቀጥታ ፊት ለፊት የምናየው ተዛማጅ ነገር ላይሆን ይችላል። ከላይ ባየነው ምሳሌ የመሪው መመረጥ እና የምርት መጨመሩ ስለተገጣጠሙ ተዛማጅ (correlated)  ቢሆኑም አንዱ ግን ለንዱ ሰበብ አይደለም።  

ማጠቃለያ

ስናጠቃልለው እውነትን አጥልሎ አንጥሮ ማውጣት ፈታኝ ነው፡፡ እንደ ወርቅ ሰሪ በጥንቃቄ ንፁሁን እውነት አንጥሮ ማውጣት ይጠይቃል፡፡ መልካምነትን ከብልህነት ጋር   አዋደን ስለ አለም ያለንን ዕይታ በጽኑ መሠረት ላይ እንድንገባ ምኞቴ ነው፡፡

ቸር ይቆየን

ይበቃል አበበ, 2014 ዓም

Please share this to:
Social media & sharing icons powered by UltimatelySocial