ደን እና መንግስት በኢትዮጵያ

(ዳሰሳዊ ምልከታ በ ንጉሡ በጋሻው)

በኢትዮጵያ መንግስታት ለደኑ ዘርፍ የሚሰጡት ትኩረት ሃገሪቱ በየጊዜው እንደምትከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲና ወቅታዊ ዓለም አቀፍ ደን-ተኮር አጀንዳዎች (international forest-based discourses) ይለዋወጣል። ላለፉት ሶስት ዓመታት እየተካሄደ  ካለው የ“አረንጓዴ አሻራ” ዘመቻ አንጻር ባሁኑ ወቅት በደኑ ዘርፍ የተሻለ መነቃቃት ያለ  ይመስላል። በዚህ ጽሑፍ በኢትዮጵያ መንግስታት ከደን ጋር የነበራቸውን ትስስር የሚያሳይ አጭር ታሪካዊ ዳሰሳ እና በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ  ካለው የ“አረንጓዴ አሻራ” ዘመቻ ጋር ተያይዞ እየቀረቡ ያሉ አሃዛዊ መረጃዎች (statistics) ግሽበት/ግነት ይታይባቸዋል (they are inflated/exaggerated) የሚል ምልከታዬን አቀርባለሁ።

ክፍል 1

ደን እና የመንግስታት ታሪክ በኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ነግስታት ከደን ጋር ስላላቸው ዝምድና ተጽፎ የሚገኝ ታሪክ ያለው ከአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን (1434 – 1468*) ጀምሮ ነው። ይሄውም  በሰሜን ሸዋ በአንኮበርና ጣርማ በር መካከል ከሚገኘው የወፍ ዋሻ ደን የሃበሻ ጥድ (Juniperus procera) ዘር ተለቅሞ እዚያው ከደኑ ወረድ ብሎ ካለ ደልደል ያለ ቦታ እንዲተከል አድርገዋል።  እንዲሁም ከዚሁ ደን ከተወሰደ ዘር በጊዜው የመራቆት አደጋ (deforestation) ደርሶበት የነበረው ከዛሬዋ አዲስ አበባ በስተምዕራብ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የመናገሻ ሱባ ደን ውስጥ የሃበሻ ጥድ እንዲተከል ማድረጋቸውና ሁለቱም ደኖች ጥብቅ የነገስታቱ ደን (Crown forest) ሆነው እንዲከለሉ ማዘዛቸው ይጠቀሳል።  ይህ ታሪክ ለእውነት የቀረበ መሆኑን በቅርቡ የሃበሻ ጥድ ላይ የተሰራ የዘረመል ምርመራ (genetic diversity study) ያመለክታል። ሁለቱ ደኖች ጥናቱ ውስጥ ከተካተቱ ሌሎች ደኖች በበለጠ ከፍተኛ ዝምድና (genetic similarity) እንዳላቸው አሳይቷል (Demissew Sertse, 2011)።

 ከከአጼ ዘርዓ ያዕቆብ በኋላ በተለይም ስለሸዋ ነገስታት ተጽፎ የሚገኘው ከደን ጋር የተየያዘ ታሪክ የያኔው የኑሮ ዘይቤኣቸው ለደን ጭፍጨፋ (deforestation) አስተዋፅኦ እንዳደረገ የሚያሳይ ነው። ይሄውም የዘመኑ ነገስታት ቋሚ መናገሻ (capital) እንዳልነበራቸው፣ ብዙ የጦር ዘመቻዎች ይካሄዱ እንደነበር፣ ብዙ ተከታይ ጦር (ጭፍራ) እንደነበራቸው እና በየቦታው ሰፈራ ሲያደርጉ ጊዜያዊ መጠለያ ለመቀለስ እንዲሁም ምግብ ለማብሰል (ግብር ለማውጣት) ለማገዶነት ብዙ ደን መጨፍጭፍ ያስፈልጋቸው ነበር። በዚህም ምክያት የደኑ ሽፋን ከጊዜ ወደጊዜ በማሽቆልቆሉ በተለይም የማገዶ እንጨት እጥረት ነገስታቱን ይፈትናቸው ነበር። በዋናነት የማገዶ እንጨት ፍለጋም መናገሻቸውን ከቦታ ቦታ ማንቅሳቀስ ግድ ይላቸው ነበር። ይህ የመናገሻ ዙረት (wandering capitals) እስክ አጼ ምንሊክ ዘመን ቀጥሎ ከአንኮበር መጀመሪያ ወደእንጦጦ ቀጥሎም ወደ አዲስ አበባ እንዲዘዋወሩ አድርጓቸዋል። በዚሁ የማገዶ እንጨት እጥረት የተነሳ ከአዲስ አበባም ወደምዕራብ ሸሽተው አዲስ ዓለም ላይ መናገሻቸውን ሊያቋቁሙ በተቃረቡበት ወቅት ነው የባህርዛፍ (eucalyptus) ከወደ አውስትራሊያ መጥቶ  አዲስ አበባን በመናገሻ ከተማነቷ እንድትቀጥል ያደረጋት።

ታሪኩ እንዲህ ነው።  አዲስ አበባ በተመሰረተች ገና በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ የማገዶ እንጨት በከተማዋ ጠፋ፤ እጅግ ውድም ሆነ። በዚህም የተነሳ አጼ ምንሊክ ደን ወደሚገኝበት ወደምዕራብ ማፈግፈጋቸውን ቀጥለው በአዲስ ዓለም መናገሻቸውን ለመትከል እንቅስቃሴ ጀመሩ። በመጨረሻም አዲስ አበባን ከመፍረስ ያዳናትና በመናገሻነቷ ጸንታ እንድትቆይ ያደረጋት የባህርዛፍ መምጣት ነበር። በ1894 ዓ.ም. Mondonvidailhet የተባለ የአጼ ምንሊክ ፈረንሳዊ አማካሪ የመጀመሪያውን የባህርዛፍ ዘር አምጥቶ አዲስ አበባ ላይ አራዳ ጊዮርጊስ ቤ/ክ አካባቢ እንደተከለ ይታመናል (Chojnacki, 1963) ። ይህ በእድገቱ ፈጣን የሆነ የዛፍ ዝርያ ወዳውኑ በከተማዋ በመስፋፋት የማገዶና የቤት መስሪያ እንጨት እጥረትን መቅረፍ ቻለ። እንዲህ እያለ በቦታው የነበሩ አገር በቀል የዛፍ ዝርያዎች (indigenous tree species) ጠፍተው ከተማዋን በባህርዛፍ የተወረረች ከተማ (Eucalyptopolis) አስባላት። ወደሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎችም በፍጥነት በመዛመት ባህርዛፍ ዛሬም ድረስ በስፋት የሚተከል የዛፍ ዝርያ ሆነ። የብዝሃ ሕይወትን (biodiversity) በመቅነስ፣ በአፈር መሸርሸርና ውሃን በማድረቅ አካባቢ ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ የማገዶና የቤት መሰሪያ እንጨት ፍላጎትን በማሟላት ባህርዛፍ ለኢትዮጵያውያን የዋለው ውለታ አሌ የማይባል ሃቅ ነው። ምናልባትም ባሁኑ ጊዜ አልፎ አልፎ በየተራራው ላይ ጭል ጭል የሚሉ የተፈጥሮ ደኖች (remnant natural forests) ጨርሰው ከመውደም የታደጋቸው ባህርዛፍ ሳይሆን አይቀርም።

ከላይ የተጠቀሱት በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ እና በአጼ ምንሊክ ዘመነ መንግስት የተከወኑ ደን-ተኮር የጥበቃና ማልማት ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ መደበኛ የደን ፖሊሲ (formal forest policy) ትግበራ የተጀመረው ግን በ 5 ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ጊዜ እንደሆነ ዶ/ር አልማዬሁ ነጋሳ “Historical development of forest policy in Ethiopia” በሚል የምርምር ጽሑፋቸው ያስረዳሉ። ጣሊያኖቹ Milizia forestale (Forest militia) የተባለ ደንን ለማስተዳደርና ለመበዝበዝ የሚውል መመሪያ አውጥተው ነበር። ነገር ግን መመሪያውን ብዙም ሳይተገብሩት በሽንፈት አገር ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል። ከዚያ በኋላ ከስደት ወደዙፋኑ የተመለሰው የአጼው መንግስት  ኢትዮጵያን የምዕራብያውያንን ሞደል በመጠቀም ማዘመን የሚል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀረጸ። ትልልቅ ገበያ ተኮር እርሻዎችን (commercial agriculture) ማስፋፋት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሆነ። በዚህ ሳቢያ ደን አንድም ጣውላው ተሸጦ የሰፋፊ እርሻ ፖሊሲውን ለመተግበር የሚሆን ገቢ ለማስገኘት፣ ሁለትም ለሚስፋፋው እርሻ ቦታ ለመልቀቅ እንደጠፍ መሬት (wasteland) ተቆጥሮ በስፋት ተመነጠረ። በተጨማሪም ንጉሡ በ 5 ዓመቱ ጦርነት ወቅት የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ በሚል በመቶና በሺ ሄክታሮች የሚቆጠር የደን መሬት ለንጉሣውያን የቤተሰብ አባላትና ባለሟሎች፣ ከጦርነት ለተመለሱ አረበኞችና ለመንግስት ሰራትኞች ያለስስት አከፋፈሉ። አዲስ ባለመሬቶችም ደኑን መንጥረው ወደእርሻ መሬት እንዲቀይሩ ይበረታቱ ነበር። ይህ ሁኔታ ያኔ ጥቅጥቅ ያለ ደን በነበራቸው የደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የተባባሰ ነበር። በዚህ ምክንያት የሃገሪቱ የደን ሽፋን እያሽቆለቆለ በመሄዱ ጉዳዩ ያሳሳባቸው የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾችና አማካሪ የነበሩ የውጭ ሃገር የደን ባለሞያዎች (በተለይም ያኔ ሃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ይሠራ የነበረው አየርላንዳዊው H. F. Mooney) ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ መሆኑንና በፍጥነት የደን ጥበቃ አዋጅ እንደሚያስፈልግ መከሩ። ከብዙ ውትወታና ውጣውረድ በኋላ የያኔው ፓርላማ በ 1965 ደካማ/ልል የሆነ የደን ህግ ቢያጸድቅም በተለያዬ ምክንያት ተጓቶ ተፈጻሚነት ሳያገኝ ዘውዳዊው አገዛዝ ሊወድቅ ችሏል።

የዘውዳዊ አገዛዙን ጥሎ መንግስታዊ ስልጣኑን የተረከበው ደርግ ለደን ጥበቃና ልማት የሰጠው ትኩረት በአመዛኙ በበጎ ጎኑ የሚጠቀስ ነው። እንደውም አንዳንዶች ለኢትዮጵያ የደን ዘርፍ ወርቃማው ዘመን (the golden age of Ethiopian forestry) ነበር ይላሉ። ወታደራዊው መንግስት ወደ ስልጣን እንደመጣ “መሬት ላራሹ” ታወጀ። ከፊውዳላዊ የመሬት ከበርቴዎችና ንጉሣውያን ቤተሰቦች ከተወረሰው መሬት የተወሰነውን በመንግስት ወደሚተዳደር የተተከለ ደን (State-owned plantation forest) ቀየረው። ደርግ ሰልጣን በያዝ በሁለት ዓመት ውስጥ እስካሁን በጠንካራ ተቋምነቱ የሚጠቀሰውን የደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን (Forest and Wildlife Conservation and Development Authority) አቋቋመ። በባለስልጣኑ መሪነትም ለማገዶና ለተለያዩ የጣውላ ምርት የሚያገለግሉ ፈጣን እድገት ያላቸው እንደ ባህርዛፍና የፈረንጅ ጥድ ያሉ ዝርያዎች (eucalyptus, cypress and pines) በስፋት ተተከሉ። መንግስት ለደኑ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ያኔ በ1970ዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ ከነበረው የነዳጅ ቀውስ (fuel crisis of the 1970s) ጋር በመገጣጠሙና ከእንጨት ለሚገኝ ኃይል (biomass energy) ከፍተኛ ትኩረት በመሰጠቱ ከለጋሾች ተጨማሪ በጀት እንዲገኝና እነዚህን ተከላዎች የበለጠ እንዲያስፋፋ አግዞታል። በመሆኑም አሁን በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሰፋፊ የተከላ ደኖች አብዛኞቹ ያኔ የተቋቋሙ ናቸው። ከደርግ ዘመን የደን ፖሊሲ እንደድክመት የሚወሰዱት የደን አስተዳደሩ በግዴታ ከላይ ወደታች የተጫነ (authoritarian top-down approach) መሆኑና ተከላዎቹ የአካባቢ ጥበቃን ያላማከሉ የውጭ አገር ዝርያዎች ላይ ብቻ ያተኮሩ (production forestry based on fast-growing exotic species) መሆናቸው ነበር። በተለይም የደን ጥበቃው ህብረተሰቡን ያላሳመነና ጥብቅ ክልከላ ላይ ብቻ የተመረኮዘ መሆኑ ኋላ ላይ ደርግ እንደወደቀ በስፋት ለተካሄዱት የደን ጭፍጨፋዎች አስተዋፅኦ አድርጓል። በዚህ ረገድ እኔ ተወልጄ ባደግኩበት የገጠር መንደር የተከሰተውንና በህፃን አዕምሮዬ የተቀረፀውን ክስተት እስካሁን አስታውሳለሁ። የደርግን በጦርነት መሸነፍ ተከትሎ በአካባቢው የአስተዳደር ክፍተት (power vacuum) ተፈጠረ። ጥብቅ ክልከላ ሲያደርጉ የነበሩት የደን ጠባቂዎችና የቀበሌ አስተዳዳሪዎች አሁን ምንም ሊያደርጉ እንደማይችሉ የተረዳው የመንደራችን ነዋሪ መጥረቢያውን ይዞ በዚያው መንደር ወደሚገኘው ጥብቅ ደን አመራ። ለዘመናት ተጠብቆ የቆዬውን ደን ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ለማውደም አንድ ቀን ብቻ በቂው ነበር። ያኔ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች (waves of deforestation) በብዙ የሃገሪቱ አካባቢዎች እንደተከሰቱ ኋላ ላይ በንባብ ለመረዳት ችያለሁ። ለምሳሌ ያህል “Dwindling Ethiopian forests” የሚለውን የ Elias N. Stebeck ጽሑፍ ይመልከቱ።

ደርግን አውርዶ የመንግስትን መንበር የተረከበው የኢህአዴግ አስተዳደር ለደኑ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት (በተለይም በመጀምሪያዎቹ 15 – 20 ዓመታት) በአናሳነቱ የሚጠቀስ ነው። ኢህአዴግ ወደ ስልጣን እንደመጣ ያወጀው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ግብርና-መር ኢንዱስትሪ (Agricultural intensification-led industrialization) ነበር። ይህን ተከትሎ በ 2001  የወጣው የገጠር ልማት ፖሊሲ (Rural development policy and strategy) ሰነድ ለግብርናው የላቀ ትኩረት ሰጥቶ ደኑ ግን ግብርናውን የሚድግፍ (agroforestry undertaking) እንጂ ራሱን ችሎ የሚለማ ዘርፍ መሆን እንደሌለበት ይገልፃል። በዚህም ምክያት የደኑ ዘርፍ በግብርናው የተገፋ (marginalized የሆነ) ነበር ብሎ መግለፅ ይቻላል። በተጨማሪም በደን የተሸፈኑ መሬቶችን ለግብርና ኢንቨስትመንት ተብሎ ለውጭ አገርና ላገር ውስጥ ባለሃብቶች ማስተላለፍ በስፋት ይከናወን ነበር። የዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች በደቡብ ምዕራብ የሃገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል፣ በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች የተባባሱ ነበሩ።  በብዙ ሺ ሄክታር የሚቆጠር የደን መሬት በተለይም ለውጭ ሃገር ባለሃብቶች በስፋት ይተላለፍ ነበር። ከእንቅስቃሴዎቹ ስፋት አንፃር በሃገሪቱ የመሬት ቅርምት (land grabbing) እየተካሄደ ነው የሚሉ ውትወታዎች በርክተው ነበር። አነዳንዶቹ ኢንቨስተሮች እንደውም የተላለፈላቸውን የደን መሬት መንጥረው እንጨቱን ከሸጡ በኋላ ቦታው ላይ ምንም ዓይነት ኢንቨስትመንት ሳያካሂዱ ይጠፉ እንደነበር ይጠቀሳል (Desalegn Rahmato 2011, 2015; Tola Gemechu, 2018)።

ኢህአዴግ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በዚህ መልኩ የደኑን ዘርፍ ትኩረት ቢነፍገውም ከ2010 በኋላ ግን የደን ልማት እንደገና ትኩረትን ስቦ ይገኛል። ለዚህም ምክንያቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና ለመከላከል (adaptation and mitigation of climate change) ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት በመታመኑና ለጋሽ መንግስታትና ድርጅቶች ለደን ጥበቃ (forest conservation) እንዲሁም የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በደን ለመሸፈን (restoration of degraded landscapes) ትልልቅ በጀት ማፍሰስ በመጀመራቸው ነው። በዚህ ረገድ በዓለም ባንክና በተላያዩ ለጋሽ መንግስታት የሚደገፉት ደን የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ለሚያደርገው አስተዋፅኦ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ መዋቅሮች (like clean development mechanism(CDM) and REDD+) በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። የኢትዮጵያ መንግስትም የኢኮኖሚ ፖሊሲውን እስከ መከለስ ደረሰ። የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ (Climate-resilient green economy strategy) አዲሱ የሃገሪቱ ትኩረት አቅጣጫ ሆነ። ደንን መጠበቅና መልሶ ማልማትም (conserving and re-establishing forests) ከአራቱ የአዲሱ ፖሊሲ ምሰሶዎች አንዱ ((one among the four key pillars MEFCC, 2018) ሆነ። ይህንን ተከትሎም የዛፍ ችግኝ ተከላ ዘመቻዎች በስፋት መካሄድ ጀመሩ። ይሄው እንቅስቃሴ “ከ2018 የመንግስት አስተዳደር/አመራር ለውጡ” በኋላም ቀጥሎ ከ2019 ክረምት ጀምሮ በሃገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር የሚመራ  የ“አረንጓዴ አሻራ” ዘመቻ (Green legacy campaign) እየተካሄደ ይገኛል። ይህ በደኑ ዘርፍ የፈጠረው መነቃቃት መልካም ሆኖ ሳለ በየዓመቱ በተከላ አሳክትናል ተብሎ በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርበው ሪፖርት እጅግ የተጋነነ ነው የሚል አመለካከት አለኝ። በቀጣዩ ክፍል በዚህና በሃገሪቱ የደን ሽፋን ላይ የተዛቡ/የተጋነኑ ናቸው በምላቸው አሃዛዊ መረጃዎች ላይ የእኔን አመለካከት ለመተንተን እሞክራለሁ።


*ከማጣቀሻ ምንጮቹ ጋር ይስማማ ዘንድ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ያሉ ሁሉም ዓመታት እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ናቸው።

Please share this to:

5 Replies to “ደን እና መንግስት በኢትዮጵያ”

  1. It is an interesting article but the the historical perspective needs to be supported by evidence. In Part I (second paragraph) you mention about “wandering capitals” due to fuel shortages? Where is the source for this information?( Could you please cite any document supporting this claim).

    1. Hi Dereje, good to hear from you.
      Thanks for your critical comment. You are right; I should have cited the source. The source I used is the following:
      Chojnacki, S. 1963. FORESTS AND THE FORESTRY PROBLEM AS SEEN BY SOME TRAVELLERS IN ETHIOPIA. Journal of Ethiopian Studies, Vol. 1, No. 1 (January 1963), pp. 32-39.

      I can attach the pdf document in case you cannot access it online.

      Thanks again!

      Nigussu

  2. It is interesting work. Keep it up. Please try to come with the pros and cons of the exotic forest expansion.

  3. Thanks, Arega for the compliments. Hopefully, I will come up with another article about the exotics.

Comments are closed.

Social media & sharing icons powered by UltimatelySocial